የሙት ባህር ጥቅሎች(The dead sea scrolls):
- aklil ዘኢየሱስ
- May 20, 2021
- 4 min read
የሙት ባህር ጥቅሎች ሲባል መስማት ያው የተለመደ ነው። እንግዲህ በ1940ዎቹ አካባቢ የተገኘው ይህ ግኝት ላይ የተወሰነ ግንዛቤ እንዲኖረን አንዳንደ ነገሮችን እናንሳ፡ አስቀድመን ስለ ግኝቱ ስናነሳ እንዳልነው በ1940ዎቹ ውስጥ በሙት ባህር ዳርቻ ከቤዱኢን ጎሳ የሆነ አንድ እረኛ ፍየሉ ትጠፋበትና እሷን በሚያፈላልግበት ወቅት ወደ ዋሻ ውስጥ እንደገባችበት በመረዳት ወደዛ ዋሻ ቀርቦ ፍየሏ ትወጣ ዘንድ ወደ ዋሻ ውስጥ ዲንጋይ ይወረውራል። በዚህ ሰዓት ግን ይህ እረኛ ባልጠበቀው መልኩ በወረወረው ዲንጋይ ሸክላ ሲሰበር ይሰማና ገብቶ ለመመልከት ይሞክራል በዚህ ሸክላ ውስጥም የነበረው ጥንታዊ ጥቅሎች ነበር። ከዚህ በኋላብ እኚህ ጥቅሎች ይህ ጎሳ ይኖርበት በነበረበት አካባቢ በተለይም ከ1947ዓም ጀምሮ ገበያ ላይም መቅረብ ጀመሩ። የእነዚህ ጥቅሎች ጉዳይም በሌሎች አለማት ላይም ተሰማ። ታሪኩን ለማሳጠር ያህል በዚህ እረኛ የተጀመረው ይህ ግኝት በዛ ቦታ ላይ ሌሎችም ጥቅሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በማሰብ በአርኪዮሎጂስቶች ምርምር ተደረገበት ምርምሩም አጥጋቢ ነበር አሥር ዋሻዎች የተገኙ ሲሆን እያንዳንዳቸው ውስጥ ብዙ ጥቅሎች ተገኝተዋል።
ከእነዚህም ጥቅሎች 4ኛው ዋሻ ውስጥ የተገኙት ብዙውን ቁጥር ይይዛሉ። ከእነዚህ ከተገኙት አጠቃላይ ወደ 930 ከሚሆኑ ጽሑፎች ውስጥ ከ25 ፐርሰንት በላዩ ቅዱሳት መጽሐፍት ናቸው። እነዚህም ጽሑፎች ከ200 ዓመት ቅ.ል.ክ እስከ 100ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ የተጻፉ እንደሆኑ ተመራማሪዎቹ ይገልጻሉ። እነዚህ መጽሐፍት በእነማን ተጻፉ ወይም ደግሞ በእነማን ተይዘው እንደነበረ ማወቁ ደግሞ ለምናነሳው ሃሳብ ጠቃሚ ነውና ስለ እነዚህ ሰዎች እናንሳ፡ ኤሤይ(essenes): ጆሴፈስ የተባለው በመጀመሪያው ክ/ዘመን የነበረው አይሁዳዊ የታሪክ ጸሐፊ በአይሁዶች ዘንድ ሦስት ክፍሎች እንደነበሩና እኚህም ደግሞ ሰዱቃውያኑ ፣ ፈሪሳውያኑ እና ኤሴይዎች እንደሆኑ ይናገራል። ታድያ ግን ከእነዚህ ሦስት ክፍሎች(Sects) ኤሴይዎች እጅጉን የተለዩ ነበሩ። ሥርዓታቸው ሕይወታቸው ሁሉ ከሌሎቹ ክፍሎች የተለየ እንደነበር ይናገራል። እርስ በእርሳቸው ያላቸው ፍቅር እጅጉን ያስገርም ነበር። በእነርሱ ማሕበር ውስጥ አንዱ ለሌላው የሚሸጠው ወይም ደግሞ ሌላው ከሌላው የሚገዛው ነገር የለም። ምክኒያቱም “የእኔ” የሚባል ነገር በእነርሱ ዘንድ አልነበረም። ሁሉም በሕብረት ነው የሚኖሩት። ይህ ደግሞ የመጀምሪያዎቹን ክርስቲያኖች ኑሮ ያስታውሰናል(ሐዋ 4፡32)። ታድያ እነዚህ ሰዎች በጣም የሚያስገርመው ሃሳባቸው ሁሉ ቅድስና እንጂ ሥጋዊ አምሮቶች አልነበሩም። ጆሴፈስም በመገረም እንዲህ ይላል፡ “ለእግዚአብሔር ያላቸው ቅድስና ፍጹም ያልተለመደ ነው ፤ ጸሃይ ከመውጣቷ በፊት ምንም ዓይነት ዓለማዊ የማይጠቅም ወሬን አይናገሩም ፤ ይልቁንም ከአባቶቻቸው የተቀበሉትን ጸሎት ያደርጋሉ። ጸሃይ ከወጣች በኋላም ሁሉም ወደ ሥራ ይወጣል እስከ 11 ሰዓትም ጸሃይ እስክትጠልቅ ይሰራሉ። በቀዝቃዛ ውኃ ታጥበው ነጭ ከለበሱ በኋላ ሁሉም በሕብረት ሆነው በአንድ ቤት ውስጥ እራትን ይመገባሉ። ሌሎች የአይሁድ ክፍሎች እንኳን በዚህ ቦታ ላይ አይቀላቀሉም። ልክ በቅዱስ ቤተ መቅደስ ውስጥ እንዳለ ንጹሕ ስብእና ባለው ሥርዓት ያከናውናሉ” በማለት ይናገራል ጆሴፈስ።[1] ይህ ደግሞ ምናልባትም ካስተዋልነው የክርስቲያኖችን ሥራዓተ ቁርባን የሚመስል ነገር አለው። እነዚህ ሰዎች በቅድስና ውስጥ እንደ መላእክት ሆነው ይኖሩ እንደነበረና ትንቢቶችንም ይናገሩ እንደነበሩ ይነገራል። እንዲሁም ሃሰት በእነርሱ ዘንድ የተጠላ በመሆኑ መሃላም በእነርሱ ዘንድ የተከለከለ ነበር። ይህም ክርስቶስ ጌታችን “አትማሉ” ያለውን ትእዛዙን ያስታውሰናል። ለሌላ ሰው ያላቸው ርህራሄና ምህረት እንዲሁም የዋሕነታቸውና ለሌላው መኖራቸው ያስገርማል። ሕይወታቸው የክርስቲያኖችን ይመስል እንደነበረ ይነገራልም ግልጽም ነውም በእውነት። ይህንን በመያዝ Christian D. Ginsburg የተባሉ አስቀድሞ አይሁድ የነበሩ ጸሐፊ ጌታችን ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ያነሳቸው ሃሳቦች የእነዚህ የኤሴይዎች መገለጫን እንደሚመስሉ በመናገርና እንዲሁም ክርስቶስ በምድር በተመላለሰበት ወራት ጸሃፍትን ፣ ፈሪሳውያንን እና ሰዱቃውያኑንም እየተቸ ሲናገር ስለ ኤሤዮች ግን ምንም አለማለቱ ክርስቶስ ያስተምር የነበረውን አይነት ሕይወት ለመኖር የሚጥሩ ሰዎች እንደነበሩ ያሳያል በማለት በመናገር የክርስትናን ሕይወት ከኤሤዮች ሕይወትና ትምሕርት ጋር በማነጻጸር ይናገራል። ታድያ ይህ ሰው ክርስቶስ ኢየሱስ ራሱ ከአይሁድ እንደመምጣቱ ሊሆን የሚችለው ከሦስቱ ክፍሎች አንዱ ነውና ከኤሤዮች ሊሆን ይችላል በማለት ይናገራል።[2] ሌላው በጣም የሚያስገርመን ነገር የእግዚአብሔር ልጅን አጥብቀው መጠባበቃቸው ነው። ይህም ለምሳሌ በአራተኛው ዋሻ (cave 4) ከተገኙ ጽሑፎች ውስጥ አንድ የአረማይክ ጽሑፍ ስለሚመጣው መሲሕ “የእግዚአብሔር ልጅ” ፣ “የልዑል ልጅ” በማለት እና ለዘላለምም እንደሚገዛም ይናገራል ይህም በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 1 ላይ መልአኩ እመቤታችንን ሲያበስራት ስለሚወለደው ጌታ ከተናገረው ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነገር ነው። እንዲሁም በ11ኛው ዋሻ (cave 11) የተገኘው የመልከጸዴቅ ጥቅል (Melchizedek Scroll) ተብሎ የሚታወቀውም ጥቅል “ይቅር የማለትና ሰይጣንን የመርታት ኃይል ስላለው የእግዚአብሔር መሳይ መገለጥ ይናገራል።”[3] አቡነ ጎርጎርዮስ በረከታቸው ይደርብንና ስለ ኤሤዮች እንዲህ አሉ፡ “ኤሤይ የሚባሉት (የአይሁድ) ክፍሎች ከፈሪሳውያኑ የሚለዩት ፈሪሳውያን (መሲሕ ሲመጣ) በጦር ኃይል ነጻ እንወጣለን ሲሉ ፤ ኤሤይ የሚባሉት ደግሞ በተዓምራት በእግዚአብሔር ኃይል ፍልስጤም ነጻ ትወጣለች ብለው ያምኑ ነበር። በቤተልሔም በስተደቡብ ልዩ ስሙ ኩምራን በሚባል ቦታ የሚኖሩ እነዚህ ሰዎች መጽሐፍትን በመጻፍ ጸሎትን በማድረስ ብዙ ጊዜ ቆይተዋል።”[4] በኩምራን አካባቢ ይኖሩ የነበሩ እኚህ ኤሴዮች በዚሁ በኩምራን ዋሻዎች ውስጥ የተገኙ ጥቅሎች ባለቤት እንደሆኑ ይታመናል። ታድያ በ1940ዎቹ ግኝት መሰረት ከእነዚህ አይሁዳውያን ላይ ከተቀበልናቸው መጽሐፍት መካከል አሁን ፕሮቴስታንቱ የማይቀበሏቸውንም ጭምር በመሆኑ ይሄ ግኝት እጅጉን እንዲስበን ያደርገዋል ምክኒያቱም እንደ ማስረጃ እንጠቅሰዋልንና። ከላይ እንደተመለከትነው ኮኸን ሻዬ የተባለው የአይሁድ ራቢና የታሪክ ምሁርም በኩምራኖች(ኤሴዮች) ዘንድ የነበረው የመጽሐፍት ብዛት በኋላ ከተነሱ ከነ ጆሴፈስና ራቢዎች ከፍ ያለ እንደነበረ መግለጹን አይተናል። በዚህ እነርሱ ሲኖሩበት ከነበረው አካባቢ ከተገኙ መጽሐፍቶቻቸው መካከል ደግሞ እነ ሲራክ ፣ ጦቢት ፣ ተረፈ ኤርሚያስ ፣ ሄኖክ እና ኩፋሌን ያካትታል። በተለይ ከዚህ ግኝት በፊት ብዙ ሊቅ ነን ባዮች መጽሐፈ ጦቢትን ከ1ኛው እስከ 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ባለው ውስጥ እንደተጻፈ ሲናገሩ ቢቆዩም ይህ ግኝት ግን አፋቸውን አዘግቷል ምክኒያቱም 4Qtobit[5] እደክታብ ከክርስቶስም መምጣት 100 ዓመት በፊት የተጻፈ ነውና በማለት ወደ ኢንግሊዘኛ በእውቅ ሊቃውንት የተተረጎመው የሙት ባህር ጥቅል መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።[6]
ስለዚህም የአይሁድ ማሕበረሰብ(community) የነበሩት ኤሴይዎች ይጠቀሙበት ከነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሁን ላይ ያሉ አይሁዶችና መሰሎቻቸው ፕሮቴስታንቶች የማይቀበሉትን እኛ የምንቀበላቸውን መጽሐፍት ይዘው መገኘታቸው አንዱ ማስረጃችን ነው።
ተጨማሪ ማስረጃዎችን ተመልሰው ይመልከቱ
ማጣቀሻዎች/Refrences
[1] The wars of jews, Bk. 2, chap 8 (ስለ ኤሤይዎች ጆሴፈስ የተናገራቸውን ጠቅላላ እዚሁ ክፍል ላይ የሚገኙ ናቸው) [2] Christian D. Ginsburg: The essenes: their history and doctrines, pg 24 [3] cale Clarke: The Ever-Deepening Mystery of the Dead Sea Scrolls, an internet article [4] የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፣ ገጽ 19 [5] 4Qtobit ይሄ የጥቅል ስም አቀማመጥ ሲሆን የእነዚህ ጥቅሎችም አነባበብ እንዲህ ነው፡ መጀምሪያ ላይ ያለችው “4” 4ኛ ዋሻ ማለት ሲሆን Q ደግሞ Qumran(ኩምራን) ለማለት ነው። ከQ በኋላ ሌላ የሚገባ ቁጥር ሲሆን የጥቅሉን ቁጥር መናገሩ ነው። [6]THE DEAD SEA SCROLLS BIBLE translated by MARTIN ABEGG, JR., PETER FLINT, AND EUGENE ULRICH, pg 378
Comentarios