ፕሮቴስታንቱ ለማይቀበሏቸው መጽሐፍት ጥንታዊ ማስረጃዎች
- aklil ዘኢየሱስ
- May 20, 2021
- 6 min read
1. ጥንታውያኑ እደ ክታባት፡ እደ ክታባቱ እጅግ ጥንታዊ ከመሆናቸው የተነሳ የጥንት ቤተክርስቲያን የትኞቹን መጽሐፍት ትቀበል እንደነበረ ትልቅ ማስረጃ ነው።
codex sinaiticus(ሳይናይቲከስ), codex vaticanus(ቫቲካነስ), codex alexandrinus(አሌክሳንድሪነስ), codex venetus(ቬኔቱስ), Codex Ambrosianus(አምብሮሲያነስ), Codex Sangermanensis(ሳንገርማነሲስ), Codex Amiatinus(አሚያቲነስ),
እኚህና የመሳሰሉት የብሉይ እና ሐዲስ ኪዳንን መጽሐፍት የያዙ እደ ክታባት የተጻፉበት ዘመን በ4ኛውና በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን አንዳንዶቹም ከዛ አለፍ ብለው ሲሆን የብሉይ መጽሐፋቸው አሁን ላይ ፕሮቴስታንቶች የማይቀበሏቸውንም መጽሐፍት ያካተቱ ነበር። [1]
እንዲሁም በ6ኛው ክ/ዘመን ተጻፈ የተባለው አንዳንዶች ደግሞ 4ኛው ክ/ዘመን ወይም ከዛም በፊት እንደነበረ የሚናገሩለት ጥንታዊ የግሪክና ላቲን እደክታብ CODEX CLAROMONTANUS(ኮዴክስ ክላሮሞንታኑስ) የጳውሎስን መልእክታትን ብቻ የያዘ ሲሆን መሃል ላይ ግን 4 ገጾች ክፍት ሆነው እዛ ላይ የብሉይ እና የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት በላቲን ስማቸው ተዘርዝረዋል። በዚህም ዝርዝር ውስጥ ፕሮቴስታንቱ የማይቀበሏቸው መጽሐፍት የተካተቱ ነበሩ።[2]
2. ጥንታውያን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜያት ይዘት፡ ያው የግሪኩ ትርጓሜ በዋናነት ሲጠቀስ እስካሁንም አይተነዋል። ታድያ ግን እነዚህን በፕሮቴስታንቱ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸውን መጽሐፍት ያካተቱ ዛሬም ድረስ ደግሞ የሚያገለግሉ ሌሎችም እጅግ ጥንታውያን ትርጓሜያት አሉ። ለዚህም የጥንቱ ግእዙ እንዲሁም የሲሪያኩ ፔሺታ የቅብጡ(Coptic) ይጠቀሳሉ።
3. ጉባኤያት፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ 3 ዓለም ዓቀፋዊ ጉባኤያት እንደተደረጉ ይታወቃል። በእነዚህ ጉባኤያት ላይ ምንም አይነት የመንጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና አልተወሰነም። እነዚህ ዓለም አቀፋዊ ጉባኤያት ላይ አባቶች ዶግማ የሆኑ ጉዳዮችን ወስነው ተለያይተዋል። ታድያ ግን በየሃገራቱ ባሉ ሲኖዶሶችም ደግሞ ጉባኤያት ይደረጉ ነበር። በእነዚህ ጉባኤያት ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና ጉዳይ ከተነሳባቸው ውስጥ አንስተን ለማየት ያህል የሮሙ ጉባኤ(382ዓም)[3] ፣ የ393ዓም የሂፖ ጉባኤ( Synod at Hippo)[4] ፣ በ419ዓም የተደረገው የካርቴጁ ጉባኤ[5] ላይም የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖናትን እነዚህ ናቸው ብለው ሲያስቀምጡ እንዲሁ በፕሮቴስታንቱ ተቀባይነት የሌላቸውንም ሲያካትቱ እናያለን። 4. በሐዲስ ኪዳንና በብዙ አባቶችም መጠቀሳቸው፡ ፕሮቴስታንቱ ከተቀበሏቸው መጽሐፍት ውስጥ እንደነ ዕዝራ፣ መኃልየ መኃልይ፣ ሩት፣ አስቴር፣ ዜና መዋዕል፣ መክብብንም ጨምሮ በሐዲስ ኪዳን በጌታም ሆነ በሐዋርያት ያልተጠቀሱ ሲሆኑ ፕሮቴስታንቱ ከማይቀበሏቸው ግን ብዙ ሲጠቀስ እንመለከታለን። እርግጥ ነው በሐዲስ ኪዳን ያልተጠቀሱት መጽሐፍት ትክክለኛ አይደሉም ማለት አይደለም። ግን ደግሞ እነዚህ በፕሮቴስታንቱ ዘንድ ተቀባይነት ከሌላቸው መጽሐፍት ውስጥ በሐዲስ ኪዳን መጽሐፍትም መጠቀሳቸው እንዲሁም በኋላ በተነሱ አባቶችም ተጠቅሰው እንደ ማስረጃ ጥቅም ላይ መዋላቸው አንዱ ሌላው ማስረጃ ነው።
በሐዲስ ኪዳን መጽሐፍ ለመጠቀሳቸው ጥቂት ማስረጃዎች፡
A. “ኑ ጻድቁን እንግደለው፤ በእኛ ጭንቅና ጽኑዕ ሆኖብናልና፤ ሥራችንንም ይቃወማልና፤ ሕግ በማጣታችንም ያሽሟጥጠናልና፤ የትምሕርታችንንም በደል ይሰብካልና። ‘እግዚአብሔርንም ማወቅ በእኔ አለ’ ይላል። ራሱንም የእግዚአብሔር ልጅ ያደርጋል [....] እግዚአብሔርም አባቱ እንደሆነ ይመካል [....] እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆነ ያድነው፤ ከሚቃወሙትም እጅ ይታደገው።” (ጥበብ 2፡12-18)
በእውነት ይህንን ጥቅስ ስናነብ ብሉይ ኪዳንን ሳይሆን ሃዲስ ኪዳንን የምናነብ ነው የሚመስለው። ታላቅ ትንቢት። ጌታ ብዙ ቦታ ላይ ፈሪሳውያኑን ሲወቅስ እናየዋለን። እንዴት የእግዚአብሔርንም ሕግ እንድሚጥሱ እያነሳ ሲናገር አይተናል። በተለይ “ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ያደርጋል” የሚለውን ቃል ይዘን ዮሐ 5፡18 ላይ “እራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ። እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር።” የሚለውን ቃል ስንመለከት እና “የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆነ ያድነው” የሚለውን ይዘን በማቴ 27፡43 ላይ “የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎአልና ከወደደውስ አሁን ያድነው።” ብለው የዘበቱበትን ቃል ስናይ ቀጥታ ትንቢቱ እንደተፈጸመ እናያለን። እውን እንዲህ ያለ ትንቢት ሰዎች ከራሳቸው አንስተው ይናገራሉ ወይ..?? ያውም ስለ ጌታ..?? በእውነት መለኮታዊ መጽሐፍ እንደሆነ ግልጽ ነው ብቻ ሳይሆን ይህንን መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ ስለ ጌታ የተናገረውን ቃል አለመቀበልና መቃወም በራሱ ምንጩ ከሃሰተኛው መንፈስም ጭምር እንደሆነ ያመለክታል።
B. “የምትወዱኝ ሰዎች ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ ከፍሬዬም ትጠግባላችሁ ... የሚመገቡኝም አይጠግቡኝም፤ የሚጠጡኝም አይሰለቹኝም። የሚሰማኝም አያፍርም ለእኔ የሚገዙ ሰዎች አይስቱም።”
በዚህ ጥቅስ ላይ ደግሞ “ለእኔ ተገዙ” የሚል የሁሉ ገዢ ጌታ በሚያስገርም ሁኔታ ግብዣ ይጠራቸዋል። ኑ ብሉኝ፤ ኑ ጠጡኝ በማለት። ይሄ በጣም ግልጽ ነው በማቴ 26፡26 ላይ ጌታችን ኢየሱስ እንጀራን ባርኮ ቆርሶ ለሃዋርያት ሲሰጣቸው “ይህ ሥጋዬ ነው” በማለት ሲሆን ጽዋውንም “ይህ ደሜ ነው” በማለት ነበር። በዮሐንስ ወንጌል 6:57 ላይ “የሚበላኝ ከእኔ የተነሳ ሕያው ይሆናል” በማለት ቀጥታ ይናገራል። ስለዚህም አስቀድሞ በሰዎች አንደበት ሲናገር የነበረው ጌታ አሁን ደግሞ ቀጥታ በራሱ ተናገረው። ማቴዎስ እንደተናገረ በተራራው ስብከት ትረካ ላይ “ያስተምራቸውም ዘንድ አፉን ከፈተ”። አስቀድሞ የቅዱሳኑን አንደበት የከፈተ አሁን ግን ቀጥታ የራሱን ከፍቶ ተናገረ።
C. በወንጌል ላይ በሙታን ትንሳኤ ዙሪያ ጌታ ሲጠየቅ አንዲት በዘር አለመተካት ምክኒያት ሰባት ወንድማማቾች በየተራ ያገቧት ሴት እንደነበረችና ሁሉም እንደሞቱ ጠቅሰው በኃላ በትንሳኤ የትኛውን እንደምታገባ ይጠይቁታል።(ማቴ 22፡25፤ ማር 12፡20) ታድያ ይህ ታሪክ የተጠቀሰው ከመጽሐፈ ጦቢት ላይ ሲሆን ታሪኩም በምዕራፍ 3 እና 7 ላይ ይገኛል።
D. ሃዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 1፡20 ላይ “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና....” በማለት የተናገረው በመጽሐፈ ጥበብ 9፡1 ላይ ካለው ቃል ጋር የሚዛመድ ነው። ቃሉም እንዲህ ይላል፡ “እግዚአብሔርን የማወቅ ጉድለት በልቦናቸው ያለባቸው ሰዎች ሁሉ በእውነት ከንቱ ናቸውና ... ሥራውንም እያዩ ሰሪውን አላወቁም”
E. ዮሐንስም በራዕዩ 1፡4 ላይ ሰላምታን ሲያቀርብ “በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት” ይላል። እነዚህ በጌታ ፊት ቆመው የሚያገለግሉ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት ናቸው። ይህንንም ቀጥታ የወሰደው ከመጽሐፈ ጦቢት 12፡15 ላይ ሲሆን ቃሉ እንዲህ ይላል፡ “በገናናውና በቅዱሱ ጌትነት ፊት ከሚቆሙ ሰባቱ መላእክት አንዱ መልአክ እኔ ሩፋኤል ነኝ” ይላል። ይህም በሉቃ 1፡19 “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ” ከሚለውና በራዕይ 8፡2 ላይ “በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ” ካለው ጋር ይዛመዳል።
በአባቶች ለመጠቀሳቸው ጥቂት ማስረጃ
A. ቀለሜንጦስ ዘሮም(25-100ዓም)፡ “የተባረከችው ዮዲት ከተማዋ በተከበበች ጊዜ ወደ እንግዶች ሰፈር ለመሄድ ከሽማግሌዎች ፈቃድ ጠየቀች፤ ለሃገሯና ሕዝቧ ካላት ፍቅር የተነሳም ራሷን ለአደጋ በማጋለጥ ወጣች፤ ጌታም ሆሎፈርኔሱን በሴት እጅ አሳልፎ ሰጠው።”[6] እንግዲህ የሮሙ ቀለሜንጦስ በስፋት እንደሚታመነው የጳውሎስ ረዳት የነበረው ቀለሜንጦስ(ፊሊ 4፡3) እንደሆነና በሮምም በሃዋርያው ጴጥሮስ እንደተሾመ ይነገራል። ምንም ጥርጥር የሌለው ነገር ግን ከሐዋርያት ከራሳቸው ቀጥታ የተማረ ሰው መሆኑ ላይ ነው። እንግዲህ ይህ የራሳቸው የሐዋርያት ተከታይ ከላይ ያለውን የዮዲትን ታሪክ ከመጽሐፈ ዮዲት ላይ አንስቶ መናገሩ መጽሐፉ በሐዋርያት ዘንድም እስትንፋሰ አምላከ ተብሎ ተቀባይነት ያገኘ ለመሆኑ ምንም አያጠራጥርም።
B. ሰማዕቱ ዮስቲን(100-165ዓም)፡ ይህ ጥንታዊ ክርስቲያን አባት ከአይሁዱ ሊቅ ከትራፎ(Trypho) ጋር ሲወያይ እንዲህ አለው “ከግብጻዊው በጥሊሞስ ጋር ሆነው ሰባው ሊቃውንት የተረጎሙትን ትርጓሜ ትክክለኛነት አንቀበልም ብለው ሌላን ለማዘገጀት የሞከሩ የአንተ መምህራን ላይ እምነትን ከመጣል የራቅሁ ነኝ፤ ከዚህም ከሰብዓ ሊቃናት ትርጓሜ ብዙ መጽሐፍቶችን አውጥተው እንደጣሉ ታስተውል ዘንድ እመኝልሃለው።”[7] አይሁድ ከጌታ መምጣት በኋላ መጽሐፍትን ቆርጠው እንዳስወገዱ ግልጽ አድርጎ ያሳያል።
C. የበርናባስ መልእክት(70-100ዓም)፡ ይህንን መልእክት ጥንት ላይ አንዳንድ ሲኖዶሶች ከሐዲስ ኪዳን መጽሐፍትም አንዱ አድርገው ይቀበሉት ነበር። ለዚህም ማሳያው በcodex sinaiticus የመጽሐፍ ቅዱስ እደክታብ ውስጥ መገኘቱ ነው። ከጳውሎስ ጋር ያገለግል የነበረው ራሱ በርናባስ እንደጻፈው የተነገረለት ይህ ጥንታዊና ተዓማኒነት የሚጣልበት ጽሁፍ እንዲህ ይላል፡ “ነቢይም በእስራኤላውያን በራሳቸው ላይ እንዲህ በማለት ተናገረ ‘ኑ ጻድቁን እንግደለው፤ በእኛ ጭንቅና ጽኑዕ ሆኖብናልና’”[8] ይህ ቃል ያው ቀጥታ ከላይ ስላየነው መጽሐፈ ጥበብ 2፡12 እየተናገረ ነው። D. ቀለሜንጦስ ዘእስክርንድርያ(150-215ዓም)፡ በሕይወታችን ውስጥ በምን መልኩ ወይም ሥርዓት መኖር እንዳለብንና ከዚህ ጋር በተያያዘ ባስተማረበት ክፍሉ ላይ ስለ “ሳቅ” ሲናገር እንዲህ አለ፡ “ ‘አላዋቂ ሰው በሳቀ ጊዜ ቃሉን ከፍ ያደርጋል’ ይላል መጽሐፍ ቅዱስ ‘ብልህ ሰው ግን በጭንቅ ከንፈሩን ፈገግ ያደርጋል’”[9] እዚህ ላይ እንደምንመለከተው “መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል” በማለት ነው የጠቀሰው። የጠቀሰው መጽሐፈ ሲራክ 21፡20ን ነው። በእውነት በዚህ ምስክርነት ይህ አባት በነበረበት በዚያን ሰዓት እንኳን ይህ መጽሐፍ ከቅዱሳት መጽሐፍት ውስጥ አንዱ ለመሆኑ ትልቅ ማስረጃ ነው።
በዚሁ መጽሐፉ ላይ ስለ “አላስፈላጊ(የተጠላ) ንግግር” ሲናገር ይህንን ጥቅስ ጠቀሰ፡ “እያወቀ ዝም የሚል ሰው አለ፤ ንግግር በማብዛትም ራሱን የሚያስጠላ ሰው አለ”[10] ይህንንም የጠቀሰው ከሲራክ 20፡5 ላይ ነው።
E. የካርቴጁ ቆጵርያኖስ(200-270ዓም)፡ ይህም አባት ስለ ምጽዋት ማብራሪያ በሰጠበት የመጽሐፍ ክፍሉ ላይ እንዲህ አለ፡ “መንፈስ ቅዱስ በቅዱሳት መጽሐፍት በኩል እንዲህ ሲል ተናገረ “’በእምነትና ምጽዋት ኃጢዓት ትነጻለች’(ጦቢት 12፡9) ... በተጨማሪም እንዲህ አለ ‘የምትነድድ እሳትን ውኃ ያጠፋታል። ምጽዋትም ሐጢዓትን ታስተሰርያለች’(ሲራክ 3፡28)”[11]
ይህ ታላቅ አባት እነዚህን መጽሐፍት መንፈስ ቅዱስ የሚናገርባቸው ቅዱሳት መጽሐፍት ይላቸዋል። ከዚህም ያለምንም ጥርጥር ከጥንትም ጀምሮ እነዚህ መጽሐፍት ከቅዱሳት መጽሐፍት የሚመደቡ እንደሆነ ግልጽ ያደርገዋል።
እንዲሁም ለቀሳውስት እና ዲያቆናቱ በጻፈው ደብዳቤ ላይም ከምስጋና በፊት ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅ ሲናገር ይህን ጠቀሰ፡
“እስካሁን ከታየው ይልቅ ሌሎች ሊጠናቀቁ የሚገባቸው ነገሮች አሉና እንዲህም ተጽፏል ‘ፍጻሜውን ሳታይ ሰውን አታመስግነው።’(ሲራክ 11፡28)”[12]
እስካሁን ያየናቸው አባቶች ከኒቂያው ጉባኤ በፊት ከነበሩት ውስጥ ሲሆን ይህም እጅግ በጥቂቱ ለማሳያ ያህል ብቻ አስቀመጥኩ። ከኒቂያ ጉባኤ በፊት የነበሩ አባቶችን ሥራዎች ፊሊፕ ስካፍ የተባለ ፕሮቴስታንት በዘጠኝ ቅጽ(volume) አድርጎ ያዘጋጃቸው ሲሆን ለምሳሌ ሁለተኛው ቅጽ ላይ ብቻ ባሉ የአባቶች ሥራ ውስጥ ከመጽሐፈ ሲራክ ብቻ 63 ጊዜ ሲጠቀስ ከመጽሐፈ ጥበብ ላይ 28 ጊዜ ተጠቅሷል። በተቃራኒው ግን ለምሳሌ ከአስቴር፣ እዝራ፣ ሩት፣ 1ኛ ዜና መዋዕል ላይ አንድም ጊዜ ሲጠቅሱ አናይም። ከነህምያም አንድ ጊዜ ብቻ ጠቅሰዋል። ታድያ ግን ይህንን ስንል እነዚህ መጽሐፍቶች አልተጠቀሱምና ቅዱሳት መጽሐፍት አይደሉም ማለት አይደለም። ሆኖም ግን ፕሮቴስታንቱ የማይቀበሏቸው መጠቀሳቸውን ከዚህ አንጻር ስንመለከተው ቃለ እግዚአብሔር ተብለው ይታመንባቸው እንደነበረ ያሳያልና ነው። ታድያ ግን በኒቂያው ጉባኤ ሰዓትና ከዛ በኋላ ደግሞ እስከ 5ኛው ክ/ዘመን ድረስ የተነሱ አባቶችንም እንዲሁ እንጥቀስ ብንል እጅግ ብዙ በጠቀስን። ግን ይሄንን እንደናሙና ይዘን ወደ ቀጣዩ እንለፍ።
5. አሁን ላይ ያሉ “የክርስትና ክፍሎች” ከሚቀበሉት አንጻር፡ እንደ ኦርቶዶክስ ያሉት.. ማለትም የሐዋርያዊት ኦሬንታልም ሆነ የምስራቆቹ እንዲሁም የካቶሊክንም ጨምሮ ከጥንት የመጡ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት በፕሮቴስታንቱ ቡድኖች ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም የተባሉትን መጽሐፍት ይቀበላሉ። ይህም ክርስትና ከተመሰረተ ጀምሮ ለ1500 ዓመታት ያህል አብያተ ክርስቲያናት ሲገለገሉበት የነበረ ነው። ታድያ ግን በኋላ ላይ ማርቲን ሉተር የቤተ ክርስቲያንን ሥልጣን ትቶ “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚል ትምሕርት ይዞ ሲመጣ ለዝች ለሥጋዊ አለም ተስማሚ ነበርና ሁሉም እየተነሳ እንደፈለገ መሆን ጀመረ። ከጥንት የመጣውንም የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ጣሉ። በእርግጥ ሉተር መጽሐፍ ቅዱስን ባዘጋጀ ወቅት የብሉይ ኪዳኑን ክፍል ከዕብራይስጥ ሲተረጉም በአይሁዳውያን ዘንድ ከመጽሐፍ የወጡትን መጽሐፍት ምንም እንኳን እንደ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ባይቀበላቸውም ግን ደግሞ ጠቃሚ ናቸው በማለት በጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱሱ ላይ ከሥር አብሮ አካቷቸዋል። በእርግጥ ከሥር ለይቶ ያስቀመጠው እነሱን ብቻ ሳይሆን ከሐዲስ ኪዳን ደግሞ እነ ዕብራውያን፣ የያዕቆብ መልእክት፣ የይሁዳን መልእክት እና የዮሐንስ ራዕይንም እንዲሁ ለይቶ ከሥር አስቀምጧል። ታድያ ግን እነዚህን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ቀስ በቀስ አሁን ላይ ያሉ ደግሞ ፕሮቴስታንቶች እንኳን መጽሐፋቸው ውስጥ ሊያካትቱት እንደውም አልፈው ሲነቅፉት መመልከት አስገራሚ ነው።
ማጣቀሻዎች/References
[1] EDMON L. GALLAGHER and JOHN D. MEADE: The biblical canon lists From early christianity_texts and analysis, chap. 6 [2] Ibid, pg 183 [3] Tylor Marshall, at www.tylormarshall.com [4] Karl Josef von Hefele: A Hstory Of The Councils Of The Church: bk.VIII Sec 109 [5] Council of carthage, canon 24: Philip schaf: NPNF s2, vol.14 [6] 1st epistle: chap. 55 [7] Dialogue with Trypho: chap. 71 [8] Epistle of barnabas, chap. 6, Philip schaff [ይህንን ጥንታዊ መልእክትና ሌሎችንም በስፋት ያዘጋጀው ፊሊፕ ስካፍ ፕሮቴስታንት ነው። ግን ደግሞ ጥሩ ዝግጅት የሚባል ነው። በዚህ መልእክት ላይ ከጥበብ መጽሐፍ መጥቀሱን ተያይዞ ሕዳጉ ላይ “This apocryphal book(Wisdom) is thus quoted as Scripture” በማለት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ መጠቀሱን ይኸው ፕሮቴስታንት አዘጋጅ ይመሰክራል] [9] The Instructor, bk. 2, chap. 5 on laughter [10] Ibid, chap. 6 on filthy speaking [11] Treatise VIII, on works and alms [12] Epistle V:2, To the Presbyters and Deacons.
ጸጋውን ያብዛልህ ወንድሜ !