ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ
(1ጴጥ 3፡1)
ፕሮ ቴስታንቲዝም
የፕሮቴስታንት እምነት የተጀመረው በ16ኛው ክ/ዘመን በማርቲን ሉተር እና በእርሱ ሰዓት በነበሩ በእነ ካልቪን በእነ ዚውንግሊ ቢሆንም ቀደም ብሎ ግን በአንዳንድ ሰዎች ለምሳሌ በእነ ጆን ዊክሊፍም የተሞከረ እንደሆነ ይነገራል። የፕሮቴስታንት መመስራት ዋናው ምክንያት በሰዓቱ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በነበሩ አንዳንድ ስህተት ትምሕርቶች ምክኒያት ነው። በሰዓቱ ካቶሊክ ጥቂት ስህተቶችን በማከናወኗ ለሉተር በር ሆነውና አረምኩ ብሎ ጭራሽ ዶግማን የሚያፋልሱ ትምሕርቶችን ይዞ ብቅ አለ። ታድያ ግን ሉተር በዛ ሰዓት ሲነሳ አሁን ላይ እንዳሉት የፕሮቴስታንት ቡድኖች በስህተት ትምሕርት ብቻ የታጨቀም አልነበረም። ምናልባትም አስተውለን ብንመለከት ማርቲን ሉተር አሁን ላይ ካሉት ፕሮቴስታንቶች ይልቅ ወደ እኛ ሳይቀርብ አይቀርም። አሁን ላይ ያለው የፕሮቴስታንት ትምሕርት እጅግ በብዙ ኑፋቄዎች የታጨቀ ከመሆኑ የተነሳ አንድ የግብጽ መምህር ምን ብሏል "በታሪክ ውስጥ በክርስትና ስም ከተነሱ መናፍቃን ውስጥ እንደ ፕሮቴስታንት በብዙ ኑፋቄ የታጨቀ የለም።" ፕሮቴስታንቶች መጽሐፍ ቅዱስን ይወዳሉ ግን አብዛኛዎቹ የተወሰኑ ጥቅሶችን ከመሸምደድ በዘለለ ውስጡን አያውቁትም። ይህ ብቻ ሳይሆን ሌላው ትልቁ ድክመታቸው መጽሐፍ ቅዱስን ሲወዱና ሲቀበሉ ሙሉ በሙሉ አይደለም። ሮሜና ገላትያ ላይ ተንጠልጥሎ የመቅረት ነገር ይታይባቸዋል። እነሱን መሰረት በማድረግ ሌላ ከእነሱ የተለዩ ሌሎች ሃሳቦችን ሌሎች መጽሐፍት ላይ ሲመለከቱ ለመቀበል ይከብዳቸዋል። ይህም ፓስተሮቻቸው በእነርሱ ላይ ያሳረፉት ከባድ እስራት ነው። ምክኒያቱም ሮሜና ገላትያ ከአውዱ ውጪ በሆነ መልኩ ይረዱታልና ነው። ይህንን መልስ በምንሰጥባቸው ጽሑፎቻችን ላይ እያስታወስናችሁ እንሄዳለን። ስለዚህም የፕሮቴስታንት ቡድኖች ኑፋቄ ውስጥ ናቸውና በእውነት "ኑፋቄ ደግሞ ያጠፋል" ተብሎ ተጽፏልና እነዚህ ወንድሞቻችን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን መልስ እንሰጣለን።
በጣፋጭ ወይን ውስጥ ገዳይ መርዝን ቀላቅለው የሚሰጡ ሰዎች አሉ። ይህንንም ያልተረዳ ሰው ከእርሱ በመጠጣት በጊዜያዊ ደስታ ሲያልፍ ነገር ግን ወደራሱ ሞት እንደሚወሰድ(በመርዙ)፤ እንዲሁ መናፍቃን የጌታችንን የኢየሱስን ስም ከመርዛቸው ጋር ቀላቅለው ይዘው ያልተገባ ነገርን ይናገራሉ። (እንዳትሞቱ ከእነዚህ ተጠበቁ)
/ ቅዱስ አግናጥዮስ(30-110 ዓም) Epistle to the Trallians, chap 5
እስልምና
እስልምና የተጀመረው በ7ኛው ክ/ዘመን መሃመድ በተባለ ሰው ነው። ይህ እምነት አጠቃላይ ትምሕርቱ ከብሉይና ከሐዲስ ኪዳን የቀጠለ እንደሆነና መሃመድ የተባለው ሰው የመጨረሻው የፈጣሪ መልእክተኛ ወይም ነቢይ እንደሆነ ያስተምራል። ቁርአን የተባለውም መጽሐፋቸው ቀጥታ ከአላህ ወደ መሃመድ ጅብሪል በተባለ መልአክ አማካኝነት በንግግር መልክ የወረደለት የመጨረሻው መለኮታዊ መጽሐፍ እንደሆነም ያስተምራል።
ታድያ ግን ምንም እንኳን ከአይሁድና ከክርስትና ጋር ተያይዞ የመጣ እምነት እንደሆነ ቢናገሩም ትምሕርቱ ሁሉ ፍጹም ከክርስቲያኖችም ጋር ሆነ ከአይሁዳውያኖች ጋር የማይስማማ እንደው በአጭሩ የማይተዋወቅ እንኳን ትምሕርት ይመስላል። ሙስሊሞች አላህንና መሃመድን እንዲሁም ቁርአኑን እጅግ ይወዳሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ በጌታችን በክርስቶስና በምስጢረ ሥላሴ ላይ እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ትምህርቶች ላይ ጥያቄዎችን ያነሳሉ። ለእነርሱም እንዲሁ "ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት የተዘጋጃችሁ ሁኑ" ይላልና ወደ እውነት ይመጡና ነጻ ይወጡ ዘንድ መልስ የምንሰጥ ይሆናል።
ሌሎች ጥያቄ የሚያነሱ አካላት
እነዚህ ምናልባትም ከኦንሊ ጂሰስ(Only Jesus) ይህም በሥላሴ ከማያምኑ እና እንዲሁም ከይሃዋ ምስክሮች ወልድ ፍጡር ነው ከሚሉ ፕሮቴስታንቶች ለሚነሱና አንዳንድ ጠቅላላ ጥያቄዎች መልስ የምንሰጥበት ይሆናል።