top of page

ማሶሬቲክ ቴክስት(Masoretic Text) እና ሰብዓ ሊቃናት (ልዩነት)

ይህ ደግሞ የእብራይስጥ መጽሐፍ ሲሆን የማሶሬት ቡድን በሚባሉ አይሁዳውያን ከ7ኛው እስከ 11ኛው ክ/ዘመን ባለው አካባቢ ውስጥ የተጻፉ እደክታባት ስብስብ እንደሆነ ይነገራል።[1] ይህ የእብራይስጥ መጽሐፍ ምንም እንኳን ቋንቋውን እብራይስጥ ብንልም ከላይ ስንናገርለት ከነበረው አስቀድሞ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ከተጻፈበት የእብራይስጥ ቋንቋ ጋር ግን ልዩነት ነው። ስለዚህም በስመ እብራይስጥ የቀደመው የእብራይስጥ መጽሐፍ መስሎ ሊታየን አይገባም። ይህ መጽሐፍ አሁን ላይ አይሁዳውያን የሚቀበሉት የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ነው። ታናክ(Tanakh) ይሉታል። ይህም በውስጡ ከያዛቸው ሦስት ክፍሎች አንጻር ነው: Torah(የሕግ መጽሐፍት), Neviim(የነቢያት መጽሐፍት) እና Ketuvim(ጽሑፎች)። ከጌታ መምጣት በኋላ አይሁዳውያን ብዙ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍትን ቆርጠው አስወጥተዋልና በእነርሱ አቆጣጠር በውስጡ 24 መጽሐፍትን የያዘ ነው። የፕሮቴስታንቱም መጽሐፍት የሚተረጎሙት ከዚሁ ጽሑፍ ሲሆን ይህም የሆነው ከማርቲን ሉተር መነሳት ጀምሮ እንጂ ከዛ በፊት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በካቶሊኩም በኦርቶዶክሱም ይህ የማሶሬቶች ጽሑፍ ተቀባይነት አልነበረውም። ይህም የሆነበት ምክኒያት አስቀድሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረውን ነገር ሁሉ ከመቃወም የመነጨ ነው። አንዳንድ ብዙም ያላነበቡ ፕሮቴስታንት ወንድሞች ከጥያቄ ለማምለጥ ያህል ምንም እንኳን የብሉይ ኪዳን መጽሐፋቸው ከሰብዓው ሊቃናትም እንደሚተረጎም ቢናገሩም እውነታው ግን አሁን ላይ ከሚገኘው በ1008ዓም ገደማ ከተቀዳ ኮዴክስ ሌኒንጋርድ ከተባለ የማሶሬቲክ ቴክስት እደክታብ ብቻ እደሆነና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከዚህ እደክታብ በእድሜ ቀደም ከሚል ግን ደግሞ ብዙ መጽሐፍቶቹ ከጠፉበትም ኮዴክስ አሌፖ የማሶሬቲክ ቴክስት እንደሚተረጎም የራሳቸውም ሊቃውንት ይመሰክራሉ።[2] የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ቁጥርም ላይ በፕሮቴስታንቱና በሌሎቹ መካከል ልዩነት የተፈጠረው በሰብዓ ሊቃናት እና በማሶሬቲክ ቴክስት መካከል ልዩነት በመኖሩ ምክኒያት ነው። ታድያ ይህ የአዲሶቹ አይሁድ መጽሐፍ እንዲሁም የፕሮቴስታንቶች መጽሐፍ መሰረት የሆነው የማሶሬቶች ጽሑፍ ምንም እንኳን ለማነጻጸሪያነትና ለማጥናትያህል ልንጠቀምበት ብንችልም ከሰብዓ ሊቃናቱ ጋር በተዓማኒነት ሊስተካከል አይችልም።በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠብቆ የኖረ አይደለምና የመንፈስ ቅዱስ ጠብቆትም አይኖረውም። በዚህም ምክኒያት ብዙ እንከኖች ያሉበት የተበረዘ መጽሐፍ ሆኗል። ይህንንም አንዳንድ ነገሮችን እያነሳን በንጽጽር መልክ ለማየት እንሞክራለን።

የመጀመሪያው ከላይም እንዳነሳነው ይህ ጽሑፍ በአዲሱ እብራይስጥ የተጻፈ በኋላ ዘመን የመጣ ነው። በዚህም ምክኒያት የብሉይ ኪዳን መጽሐፍትን የጻፉት ቅዱሳን ሰዎች ይህንን መጽሐፍ ቢያዩት ሊያነቡት እንኳን አይችሉም ምክኒያቱም ሌላ እብራይስጥ ስለሆነ። ይህንን ያልነው ከላይም እንደተናገርነው በስመ እብራይስጥ ትልቅ ግምት እንኳን እንዳይሰጠው ነው። ባይሆን ግን ይህንን አዲስ ጽሑፍ የተወሰነ ስንመለከተው ከኦሪጅናል ዕብራይስጥ ክታቡ ጋር ቀርቶ ከላይ ከሰብዓ ሊቃናቱ ጋር ስናነጻጽር ከነበረው እብራይስጥ ጋርም ልዩነት አለው። ይህንንም ለምሳሌ በቁምራን ከተገኙ የእብራይስጥ መጽሐፍት ጥቅሎች እና ጄሮም እርሱ በነበረበት ጊዜ ከእብራይስጡ ከተረጎመው የላቲን መጽሐፍ ጋር በማነጻጸር ማየት የሚቻል ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ ሐዲስ ኪዳንን እስትንፋሰ እግዚአብሔር ነው ብሎ ለሚያምን ሰው በሐዲስ ኪዳን ላይ ከብሉይ ኪዳን የተጠቀሱ ጥቅሶችን ሄዶ መፈተሽ የግድ ይለዋልና የተጠቀሱ ጥቅሶችን እየያዝን የብሉይ ኪዳን አቻቸውን ከሰብዓ ሊቃናት እና ከማሶሬቲክ ጋር እናመሳስለዋለን።


1. ሐዲስ ኪዳን፡ (ማቴዎስ 1፡23) "እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች.."

ሰብዓ ሊቃናት፡ (ኢሳ 7፡14) "እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች.."

ማሶሬቲክ ቴክስት፡ (ኢሳ 7፡14) "እነሆ ወጣት ሴት[3] ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች.."

2. ሐዲስ ኪዳን፡ (ዕብ 10፡5) "ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ"

ሰብዓ ሊቃናት፡ (መዝ40፡6) ".... መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ"

ማሶሬቲክ ቴክስት፡ (መዝ40፡6) መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ጆሮዎቼን ከፈትክልኝ[4]"


3. ሐዲስ ኪዳን፡ (ሉቃ 4፡19) “..ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ.. ልኮኛል” ሰብዓ ሊቃናት፡ (ኢሳ 61፡1) "..ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና [..] ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ.. ልኮኛል"

ማሶሬቲክ ቴክስት፡ (ኢሳ 61፡1) "..ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና [..] ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ.. ልኮኛል"[5]

4. ሐዲስ ኪዳን፡ (ማቴ 12፡17፣21) "በነቢዩ በኢሳይያስ የተባለው ይፈጸም ዘንድ እንዲህ ሲል.. አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ።"

ሰብዓ ሊቃናት፡ (ኢሳ42፡4) "አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ።"

ማሶሬቲክ ቴክስት፡ (ኢሳ42፡4) "ደሴቶችም ሕጉን ይጠባበቃሉ"[6]

5. ሐዲስ ኪዳን፡ (ዕብ 1፡6) "የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ(ለኢየሱስ) ይስገዱ ይላል።"

ሰብዓ ሊቃናት፡ (ዘዳ 32፡43) "የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይሰግዱለታል።"

ማሶሬቲክ ቴክስት፡ [ስለዚህጉዳይምንምአይልም][7]


6. ሐዲስ ኪዳን: (ሃዋ 7፡14) "ዮሴፍም አባቱን ያዕቆብንና ሰባ አምስት ነፍስ የነበረውን ቤተ ዘመድ ሁሉ ልኮ አስጠራ።"

ሰብዓ ሊቃናት፡ (ዘፍ 46፡27) "ከዮሴፍ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት የያዕቆብ ቤተ ሰዎች ሁሉ ሰባ አምስት ናቸው።"

ማሶሬቲክ ቴክስት: (ዘፍ 46፡27) "ወደ ግብፅ የገቡት የያዕቆብ ቤተ ሰዎች ሁሉ ሰባ ናቸው።"[8]

7. ሐዲስ ኪዳን: (ሮሜ 15፡12) "ደግሞም ኢሳይያስ 'የእሴይ ሥር አሕዛብንም ሊገዛ የሚነሣው ይሆናል፤ በእርሱ አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ' ይላል።"

ሰብዓ ሊቃናት፡ (ኢሳ 11፡10) "የእሴይ ሥር አሕዛብንም ሊገዛ የሚነሣው ይሆናል፤ በእርሱ አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ።"

ማሶሬቲክ ቴክስት: (ኢሳ 11፡10) "ለአሕዛብ ምልክት ሊሆን የቆመውን የእሴይን ሥር አሕዛብ ይፈልጉታል"


8. ሐዲስ ኪዳን: (ሃዋ 7፡43) "የሠራችኋቸውን ምስሎች እነርሱንም የሞሎክን ድንኳንና ሬምፉም የሚሉትን የአምላካችሁን ኮከብ አነሣችሁ.. ተብሎ እንዲህ ተጽፎአል."

ሰብዓ ሊቃናት፡ (አሞ5፡26) "ለራሳችሁም የሠራችኋቸውን ምስሎች፥ የሞሎክን ድንኳንና የአምላካችሁን የሬፋን ኮከብ አነሣችሁ።"

ማሶሬቲክ ቴክስት: (አሞ5፡26) "ለራሳችሁም የሠራችኋቸውን ጣኦታት ቺኡንን ንጉሳችሁን ሲኩትን የአማልክቶቻችሁንም ኮከብ አነሣችሁ።[9]


9. ሐዲስ ኪዳን፡ በሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ እነ ሙሴ የተሻገሩት ባህር “ቀይ ባሕር( ερυθράθάλασσα)” እንደሆነ ተቀምጧል። አንዳንድ ቦታ ላይ “ኤርትራ ባህር” ቢባል “ቀይ” የሚለውን ቃል የሚተካውን የግሪኩን ቃል ερυθρά(ኤሩትራ) ቀጥታ ቃሉን ሳይተረጉሙ ከግሪኩ በመውሰድ እንደሆነ ልብ ልንለው ይገባል።

(ሃዋ 7፡ 36 ፤ ዕብ 11፡29)


ሰብዓ ሊቃናት፡ በግሪኩ ብሉይ ኪዳን ላይ ቀይ ባህርን “ቀይ ባህር” ይለዋል። ስለዚህም ቀይ ባህርን ቅዱስ እስጢፋኖስም ቅዱስ ጳውሎስም ያውቁታል። ምክኒያቱም የእኛ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ እና የሐዋርያት የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ተመሳሳይ ነው። ማሶሬቲክ ቴክስት፡ የዕብራይስጡ መጽሐፍ “ቀይ ባህር” የሚባል ነገር አያውቅም። ብዙዎቹ ከዚሁ የሚተረጎሙ መጽሐፍት “Red sea”(ቀይ ባህር) በማለት ቢያስቀምጡም ዕብራይስጡ ግን “reed sea”(ሸንበቆ የሚበቅልበት ባህር) ይለዋል። የዕብራይስጡን ወደጎን አድርገው ከእኛው ከሰብዓ ሊቃናት ላይ መተርጎማቸው መጽሐፋቸው የተበረዘና ብዙ ስህተቶችን የያዘ እንደሆነ እየመሰከሩልን ይመስላል።


ስለዚህም የሐዋርያቱ ብሉይ ኪዳን መጽሐፍ እና የፕሮቴስታንቱ ወይም አሁን ያሉ የአይሁዳውያኑ ብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ይለያያል ማለት ነው።

ማጣቀሻዎች/References

[1] Emmanuel tov: textual criticism of the Hebrew bible, 2nd ed. Pg 22 [2] THE DEAD SEA SCROLLS BIBLE translated by MARTIN ABEGG, JR., PETER FLINT, AND EUGENE ULRICH, pg 9

[3] እዚህ ላይ የፕሮቴስታንቶች መጽሐፍትም እንደ እኛው “ድንግል” ብለውታል። ይህ ግን ከሚተረጉሙበት የእብራይስጥ መጽሐፍ ላይ ያገኙት አይደለም። ይልቁንም ከሰብዓ ሊቃናት ላይ የተኮረጀ ነው ማለት ይቻላል። በዚህም ምክኒያት የእነሱ መጽሐፍ የተበረዘ እንደሆነ እነርሱም ምስክር እየሆኑን ነው ማለት ይቻላል። በእብራይስጡ ስላለው ስለ ትክክለኛው ቃል ግን አይሁዶች በኢንግሊዘኛውም ትርጓሜያቸውም ላይ “Young Woman” ነው ያሉት(JPS Hebrew-english tanakh)። ፕሮቴስታንቶች ስለ ብሉይ ኪዳን መጽሐፍ መናገር ያለባቸው አይሁዶች እንደሆኑ ያስባሉ ግን ደግሞ መልሰው የአይሁዳውያኑን ወደ ጎን ሲያደርጉ እናያለን። [4] እዚህ ጥቅስ ላይ ደግሞ እኛ ሃገር ያለው የፕሮቴስታንቶች መጽሐፍ ከራሱ ከሚተረጎምበት ከእብራይስጡ ብቻ ሳይሆን በውጭ ካሉት የኢንግሊዘኛ የፕሮቴስታንት መጽሐፍቶችም ሳይቀር ተለይቶ ያው ከእኛው ተወስዶ መጽሐፋቸው ውስጥ “ሥጋን አዘጋጀህልኝ” የሚለው ተካትቷል። ይሄ ማለት የእብራይስጡ ላይ “ጆሮዎቼን ከፈትክልኝ” የሚለው ቃል እስትንፋሰ እግዚአብሔር አይደለም ማለት ነው..?? ያው የእብራይስጡ መጽሐፍ ለመበረዙ እነሱ ራሳቸው ማስረጃ ይሆኑናል። ከቃሉ ጋር በተያያዘ ግን ጠቅላላ የኢንግሊዘኛ መጽሐፍቶች እንደ ማሶሬቲክ ጽሑፉ ነው የሚያስነብቡ ሲሆን እንዲህ ይላል፡ “..My ears You have opened”(NKJV) [5] እዚህ ላይ ደግሞ ጌታ ካነበበው ከኢሳያስ መጽሐፍ ጋር የፕሮቴስታንቱ ልዩነት አለው። በጌታ ከተደረጉ ተዓምራት ውስጥ የዓይንን ብርሃን መመለስ ነበር። ይህም አስቀድሞ በትንቢት የተነገረ ሲሆንና ራሱ ክርስቶስም በምድር ላይ ሳለ ካነበበው መጽሐፍ ውስጥ የተገኘ ሲሆን የፕሮቴስታንቱ ላይ ግን ይህ ትንቢት የለም። ያው በአንድም በሌላም ምክኒያት ከመጽሐፍ ውስጥ ወጥቷል።

[6] እዚህ ላይም አሕዛብ ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም እንደሚያምኑ የተነገረበትን ትንቢት በሐዲስ ኪዳንም ተጠቅሶ ስናነበው ማሶሬቲክ ቴክስት ላይ ግን ሃሳቡም አልሰፈረም በቦታው። ታድያ ግን እንደተለመደው እዚህ ጋርም ምንም እንኳን ሌሎች ኢንግሊዘኛ ትርጉሞች እንደ ማሶሬቲኩ ቴክስት ቢተረጉሙም የእኛ ሃገሩ ላይ ግን ከእኛው ላይ ተወስዶ ተካቷል። በዚህም የማሶሬቲክ ጽሑፍ ተዓማኒነት እንደሌለው ይገልጹልናል። የኢንግሊዘኛው እንዲህ ይላል፡ “and the isles shall wait for his law”(KJV) [7] እዚህ ላይ ምንም እንኳን ጳውሎስ የጠቀሰው ጥቅስ ማሶሬቲክ ቴክስት ላይ ጭራሹኑ ባይገኝም ከዚህ በተሻለ የሚያስገርመን ግን ይህ የጳውሎስ ጥቅስ በሙት ባህር ከተገኙ የእብራይስጥ ጥቅሎች ውስጥ ዘዳግም 32፡43 ከሰብዓ ሊቃናቱ እና ከጳውሎስ ጋር ይስማማል። ይህ ማሶሬቲክ ቴክስት ግን ከጥንታውያን እብራይስጥ ጋርም ልዩነቱ ጉልህ ሆኖ የታየበት ነው። [8] “ጸጋና ኃይል የተሞላ” ተብሎ የተመሰከረለት እስጢፋኖስ በብዙ የአይሁድ ሊቃውንት ፊት ወደ ግብጽ ስለ ገቡት የያዕቆብ ቤተ ሰዎች ብዛት ሰባ አምስት እንደሆኑ ሲናገር የሰብዓ ሊቃናቱም ትርጓሜ ይስማማል። የማሶሬቲኩ ግን ሰባ ይላል። በእርግጥ ይሄ የቁጥር ልዩነት እንደ ትልቅ ግጭት ባናየውም ግን ደግሞ ጌታ ኢየሱስ ሲያነበው ሐዋርያት ሲጠቀሙበት የነበረውን መጽሐፍ የትኛው እንደሆነ እንድናውቅበት ይረዳናል።

[9] እዚህ ጋርም እንደምንመለከተው እስጢፋኖስ ጠቅሶ ከተናገረበት መጽሐፍ አሁን ላይ የፕሮቴስታንቱ መጽሐፍ ልዩ ነው። ያው እንደተለመደው እኛ ሃገር ያለው መጽሃፋቸው ላይ ግን ማሶሬቲክ ቴክስትን ገፍተር አድርገው ከሰብዓ ሊቃናቱ አስፍረውበታል። የኢንግሊዘኞቹ መጽሐፍት ግን አብዛኛው ከላይ ካስቀመጥነው ከማሶሬቲክ ቴክስቱ ጋር አንድ ነው። ለምሳሌ እንዲህ ይላል እኛ የወሰድንበት የኢንግሊዘኛ መጽሐፍ፡ “You also carried Sikkuth your king And Chiun, your idols, The star of your gods, Which you made for yourselves.” (NKJV) ይሄ ቦታ ላይ በጄሮም ሰዓት በዛ ሰዓት ከነበረው እብራይስጥ የተተረጎመው ላቲኑ ላይም ወደ ሰብዓ ሊቃናቱ በጣም የተጠጋ ሲሆን ከማሶሬቲክ ቴክስት ጋር ፍጹም ይለያል። ይህ የሚያሳየን ከላይ እንዳልነውም ማሶሬቲክ ቴክስት እነ ጄሮም በነበሩበት ሰዓት ከነበረውም እብራይስጥ መጽሐፍም እንደሚለይ ነው።


Recent Posts

See All
የሙት ባህር ጥቅሎች(The dead sea scrolls):

የሙት ባህር ጥቅሎች ሲባል መስማት ያው የተለመደ ነው። እንግዲህ በ1940ዎቹ አካባቢ የተገኘው ይህ ግኝት ላይ የተወሰነ ግንዛቤ እንዲኖረን አንዳንደ ነገሮችን እናንሳ፡ አስቀድመን ስለ...

 
 
 
የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ቀኖና

ቀኖና(canon) ማለት መለኪያ መመዘኛ እንደማለት ነው። አሁን ባለንበት ጊዜ ቀኖና ብለን ስንናገር የእግዚአብሔር ቃል የሆኑትን መጽሐፍት ካልሆኑት መለየታችን ቢሆንም ከጥንት ጀምሮ ግን የመጽሐፍት ቀኖና ሲባል ግዴታ...

 
 
 

Comments


​ከሥር ባለው ሳጥን ውስጥ ኢሜልዎትን በማስገባት "subscribe" የምትለዋን በመጫን አዳዲስ መልሶችን ቀጥታ በኢሜል ይቀበሉ

ቤተሰብ ስለሆኑን እናመሰግናለን

bottom of page