top of page

የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ቀኖና

ቀኖና(canon) ማለት መለኪያ መመዘኛ እንደማለት ነው። አሁን ባለንበት ጊዜ ቀኖና ብለን ስንናገር የእግዚአብሔር ቃል የሆኑትን መጽሐፍት ካልሆኑት መለየታችን ቢሆንም ከጥንት ጀምሮ ግን የመጽሐፍት ቀኖና ሲባል ግዴታ እንዲህ ማለት አይደለም። ይልቁንም የእግዚአብሔር ቃል በሆኑት መጽሐፍትም መካከል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚነበቡ ተብሎ በቀኖና ሊለዩ ይችላል። ይህንን ምናልባት ወደታች ግልጽ የምናደርገው ይሆናል። የብሉይ ኪዳን ቀኖና በአይሁድም ዘንድ ሆነ በክርስቲያኖች በተለያዩ አካባቢዎችና ሰዎች ዘንድ የተለያዩ አመለካከቶች የሚሰጡበት ነገር ነበር። ቀኖና በማድረግ ደረጃ አይሁዳውያን የብሉይ ኪዳንን መጽሐፍት ወስነው አያውቁም። ከጌታችን ክርስቶስ መምጣት በኋላና ከክርስቲያኖች መነሳት በኋላ ግን በተለይ የክርስቲያኖችን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት መጠቀም ጋር ተያይዞ ይሄንን አንቀበልም ያንን አንቀበልም የሚሉ ሃሳቦች ተነሱ። ከዛም በኋላ ያለምንም ትልቅ ማስረጃ 24 መጽሐፍት እንዳሉ ማወጅ ጀመሩ። ሻዬ ኮኸን(cohen, shaye) የተባለ የአይሁድ መምህር(Rabbi) እና የታሪክ ምሁር በእውቅ መጽሐፉ ላይ እንዲህ አለ፡ “አጠቃላይ የታናክ(tanakh) የቀኖና ሂደት ‘ለምን እነዚህ መጽሐፍት ተካተቱ እነዚያስ ለምን አልተካተቱም?’ የሚል ጥያቄን ያስነሳል። መክብብ ተካትቶ ለምን ሲራክ አልተካተተም? መጽሐፈ አስቴር ተካትቶ ለምን መጽሐፈ ዮዲት አልተካተተም? ዳንኤል ተካትቶ ለምን ሄኖክ አልተካተተም? እነዚህ በቀኖና ውስጥ የተካተቱትን መጽሐፍት ካልተካተቱት የሚለይ ተጨባጭና እርግጥ የሆነ መመዘኛ የለም።”[1] በማለት ከተናገረ በኋላ፡ “ስለምን ጦቢትን፣ ሲራክን እና ዮዲትን አልተቀበልንም?” በማለት ይጠይቅና “አናውቅም” በማለት ይመልሳል።[2]

ይኸው የአይሁድ ምሁር እንደተናገረው “የመጽሐፍ ቅዱስን “ቀኖና” የሚወስኑት የተወሰኑ የተማሩት(ምሁራኑ) ሳይሆኑ የአይሁድ ማህበረሰቡ(communities) ናቸው። መጽሐፉ ተቀባይነት እንዲኖረው በአይሁድ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረው ዘንድ ግድ ነው። የተለያዩ ማሕበረሰቦች ደግሞ የተለያየ ቀኖናን ይቀበላሉ። የጆሴፈስ እና የራቢዎቹ ቀኖና አጭሩ ቀኖና ሲሆን[3] የኩምራኖቹ አይሁዳውያን መጽሐፍ እና በውጭ ያሉ አይሁዳውያን(the diasporas) መጽሐፍ ቁጥሩ የሚበልጥ ነበር።”[4]

በዚህ በራሳቸው የአይሁድ ምሁር መሰረት ከክርስቶስ መምጣት በፊት የነበሩት በቁምራን አካባቢ ይኖሩ የነበሩ የአይሁድ ማሕበረሰብ እና በውጭ የነበሩት የአይሁድ ማሕበረሰቦች የሚቀበሉት የመጽሐፍ ብዛት ብዙ እንደነበረ ግልጽ ነው። የክርስቲያኖችም የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ከእነዚሁ አይሁዶች የመጣ ሲሆን ክርስቶስ አምላካችን ከመጣ በኋላ አይሁዳውያን የራሳቸውን መጽሐፍት ክደው ወይም ደግሞ ምናልባትም የጥቂት አይሁዳውያን ብቻ ተቀባይነት የነበረውን ቀኖና በመያዝ ሌሎች እስትንፋሰ አምላክ የሆኑትን መጽሐፍት ጥለዋል።

በክርስትናም ዘንድ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና ጉዳይ አጨቃጫቂ ነበር። የተለያዩ አመለካከቶችም በተለያዩ አባቶች ሲሰጡ ነበር። እጅግ ጥቂት የሚባሉ አባቶች ቀጥታ ክርስቶስ ከመጣ በኋላ የተነሱ አይሁዶችን መጽሐፍት ቁጥር በመያዝ አንዳንድ መጽሐፍትን ከቀኖና ውጭ ሲያደርጉ ነበር ምንም እንኳን አሁን ላይ ካሉ አይሁዳውያንና ፕሮቴስታንቶች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚመሳሰል ባይሆንም። ታድያ ግን በዋናነት ተቀባይነት የሚኖረው አጠቃላይ በቤተ ክርስቲያን ዘንድ በብዙዎች ይታመን የነበረውና በትውፊት የመጣው እንጂ በግለሰብ ደረጃ የተሰጡ ሁሉ ተቀባይነት አላቸው ማለት አይደለም። እንደዛ ቢሆን ኖሮ በብሉይ ኪዳን ላይ ብቻ ሳይሆን በሐዲስ ኪዳን ላይም ብዙ ልንጥላቸውና ልንጨምራቸው የምንችላቸው መጽሐፍት በኖሩ ነበር። ስለ ቀኖና ስናወራ ኮኸን ሻዬም እንደሚለው “ቀኖና ሂደታዊ እንጂ ክስተት አይደለም”( Canonization is a process, not an event)። በእርግጥ ጥንታዊ በሚባሉ አብያተ ክርስትያናት(በካቶሊክ፣ በምስራቅ ኦርቶዶክስ፣ በኦሬንታል ኦርቶዶክስ) መካከልም የቀኖና ልዩነት አለ። ታድያ ግን አንድ አስተውለን ማለፍ የሚገባን ነገር የመጽሐፍት ብዛት ወይም ቁጥር ዶግማ አይደለም። አብያተ ክርስቲያናትንም የሚለያይ ነገር አይደለም። ያው ሌላ ዶግማ የሚሰብክ በቅዱሳን ስም የተሰየሙ የመናፍቃንን መጽሐፍት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እስካላካተቱ ድረስ ማለት ነው። ይህንን ደግሞ የሚያደርግ አንድም ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን የለም። የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ላይ ፕሮቴስታንቱ 39 መጽሐፍትን ሲቀበሉ ካቶሊክ 46 መጽሐፍትን ትቀበላለች፣ የግሪክ ኦርቶዶክስ 49 ትቀበላለች የኛ ቤተክርስቲያን ደግሞ 46 ትቀበላች፤ በመካከላቸው ግን የመጽሐፍት አቆጣጠር ልዩነት አለ። በቤተ ክርስቲያናችን የብሉይ ኪዳን ቀኖና(የእግዚአብሔር ቃል) ውስጥ የሚካተቱትን ተመልክተን እዚህ ጋር እንዘርዝርና ከጥንት ጀምሮ የመጣውን ቀኖና ለመመልከት እንሞክራለን።


በዚህ ዝርዝር ውስጥ በደማቅ ያስቀመጥቋቸው በፕሮቴስታንቱ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸውን ሲሆን አያይዤ ከሰብዓ ሊቃናት የተወረሰውን የኢንግሊዘኛ ስሞቻቸውንም አስቀምጣለሁ።

1. ኦሪት ዘፍጥረት

2. ኦሪት ዘጸአት

3. ኦሪት ዘሌዋውያን

4. ኦሪት ዘኁልቁ

5. ኦሪት ዘዳግም

6. መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ

7. መጽሐፈ መሳፍንት

8. መጽሐፈ ሩት

9. መጽሐፈ ሳሙኤል 1 እና 2

10. መጽሐፈ ነገስት 1 እና 2

11. መጽሐፈ ዜና መዋዕል 1

12. መጽሐፈ ዜና መዋዕል 2

13. መጽሐፈ ኩፋሌ( Jubilees)

14. መጽሐፈ ሄኖክ(Enoch: ከላይ ለኩፋሌ ያስቀመጥነውን ሪፈረንስ ተመልከት)

15. መጽሐፈ ዕዝራ እና ነህምያ

16. መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል እና ዕዝራ 2(first and second Esdras)

17. መጽሐፈ ጦቢት(Tobit)

18. መጽሐፈ ዮዲት(Judith)

19. መጽሐፈ አስቴር

20. መጽሐፈ መቃብያን 1(Maccabees 1)

21. መጽሐፈ መቃብያን 2 እና 3(Maccabees 2 and 3)

22. መጽሐፈ እዮብ

23. መዝሙረ ዳዊት

24. መጽሐፈ ምሳሌ(እስከ ምዕራፍ 24 ድረስ ብቻ)

25. መጽሐፈ ተግሣጽ(ይህ ሌላ መጽሐፍ አይደለም፤ ከመጽሐፈ ምሳሌ የቀሩትን ምዕራፋት

የያዘ ነው።)

26. መጽሐፈ ጥበብ(Wisdom)

27. መጽሐፈ መክብብ

28. መሓልየ መሓልይ

29. መጽሐፈ ሲራክ(Sirach)

30. ትንቢተ ኢሳያስ

31. ትንቢተ ኤርምያስ ፣ ሰቆቃወ ኤርምያስ ፣ ተረፈ ኤርምያስ እና ባሮክ(Letter of

jeremiah and Baruch)

32. ትንቢተ ሕዝቅኤል 40. ትንቢተ ናሆም

33. ትንቢተ ዳንኤል 41. ትንቢተ ዕንባቆም

34. ትንቢተ ሆሴዕ 42. ትንቢተ ሶፎንያስ

35. ትንቢተ አሞጽ 43. ትንቢተ ሃጌ

36. ትንቢተ ሚክያስ 44. ትንቢተ ዘካርያስ

37. ትንቢተ ኢዩኤል 45. ትንቢተ ሚልክያስ

38. ትንቢተ አብድዩ 46. […………….] ተካትቶ አልታተመም

39. ትንቢተ ዮናስ


እኚህንመጽሐፍትበቤተክርስቲያናችንበትውፊትተቀበልን።



ማጣቀሻዎች/References

[1] Cohen, Shaye: From The Maccabees to The Mishnah 2nd ed: pg 182 [2] Ibid, pg 183 [3] እነ ጆሴፈስ ከክርስቶስ መምጣት በኋላ የተነሱ ሲሆኑ ሌሎቹ ግን ከክርስቶስ መምጣት በፊት የነበሩ እንደሆኑ ልብ ልንለው ይገባል። [4] ibid pg 184

Recent Posts

See All
የሙት ባህር ጥቅሎች(The dead sea scrolls):

የሙት ባህር ጥቅሎች ሲባል መስማት ያው የተለመደ ነው። እንግዲህ በ1940ዎቹ አካባቢ የተገኘው ይህ ግኝት ላይ የተወሰነ ግንዛቤ እንዲኖረን አንዳንደ ነገሮችን እናንሳ፡ አስቀድመን ስለ...

 
 
 
ማሶሬቲክ ቴክስት(Masoretic Text) እና ሰብዓ ሊቃናት (ልዩነት)

ይህ ደግሞ የእብራይስጥ መጽሐፍ ሲሆን የማሶሬት ቡድን በሚባሉ አይሁዳውያን ከ7ኛው እስከ 11ኛው ክ/ዘመን ባለው አካባቢ ውስጥ የተጻፉ እደክታባት ስብስብ እንደሆነ ይነገራል።[1] ይህ የእብራይስጥ መጽሐፍ ምንም እንኳን...

 
 
 

Comentarios


​ከሥር ባለው ሳጥን ውስጥ ኢሜልዎትን በማስገባት "subscribe" የምትለዋን በመጫን አዳዲስ መልሶችን ቀጥታ በኢሜል ይቀበሉ

ቤተሰብ ስለሆኑን እናመሰግናለን

bottom of page