ሰብዓ ሊቃናት ትርጓሜ(septuagint LXX)
- aklil ዘኢየሱስ
- Apr 14, 2021
- 6 min read
Updated: May 20, 2021
የሰብዓ ሊቃናቱ ትርጓሜ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ300 ዓመት ገደማ ከቀደምቱ እብራይስጥ ወደ ግሪክ እንደተተረጎመ ይነገራል። የትርጉም ሥራውም የጀመረበት ምክኒያት በእስክንድርያ ዳግማዊ በጥሊሞስ የተባለ ንጉስ ታላቅ ቤተ መጽሐፍትን በማስገንባቱ የአይሁድን መጽሐፍትም በዛው ለማካተት ሲባል እንደነበረና በትርጉም ሥራው ላይም ከ12ቱም ነገደ እስራኤል ሰድስት ስድስት ተውጣተው ሰባ ሁለት የአይሁድ ሊቃውንት እንደተሳተፉና ተዓምራዊ የትርጉም ሥራ እንደነበረ ታሪክ ይናገራል። ይህም ለምሳሌ የአርስቲያስ ደብዳቤ(The Letter Of Aristeas) ተብሎ በሚታወቀው ጥንታዊ ጽሑፍ ላይ ተገልጿል። ሰባ ሁለት ሊቃውንት ተሰባስበው ትርጉሙን ቢጀምሩም አንዳንዶች አምስቱን የሕግ መጽሐፍትን ብቻ እንደተረጎሙና ሌሎቹን ደግሞ የግሪክ መጽሐፍት ሌሎች እንደተረጎሟቸው ሲናገሩ አብዛኞቹ ደግሞ አብዛኛውን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ራሳቸው 72ቱ ሊቃውንት እንደተረጎሙት ይስማማሉ። ያም ሆነ ይህ ግን በጠቅላላው የግሪኩ ትርጓሜ መጽሐፍ[1] ሰብዓ ሊቃናት(septuagint) ተብሎ ይጠራል። ስሙም የመጣው ከላቲኑ ሰባ ቁጥር(Septuaginta, LXX.) ሲሆን ይህም ሰባ ሁለቱን ሊቃውንተ አይሁድ የሚያመለክት ነው።
የግሪክ ቋንቋ እጅጉን በተስፋፋበትና ኃያል በሆነበት በዛ ዘመን ይህ የግሪኩ ትርጓሜ እጅጉን ተቀባይነት የነበረውና አይሁዳውያን በምኩራቦቻቸው ሳይቀር ይጠቀሙበት የነበረ ነው። በሐዲስ ኪዳንም ዘመን ትልቅ ተቀባይነት የነበረው ይኸው ትርጓሜ ነው። አልፍረድ ኤደርሼይም( Edersheim, Alfred) የተባላ ፕሮቴስታንት ጸሐፊ እውቅ በሆነው መጽሐፉ(The Life and Times of Jesus the Messiah) ላይ የግሪኩን የብሉይ ኪዳን ትርጓሜ መጽሐፍ እንዲህ ሲናገርለት እንመለከታለን፡ “የተከበረ የሚያደርገው ጥንታዊነቱ ብቻ ሳይሆን ክርስቶስ በመጣ ሰዓትም የእኛን ተቀባዩንም መጽሐፍ(Authorized version)[2] ቦታ የያዘ ስለነበረም ነው። እንዲሁ በነጻነትም በሐዲስ ኪዳን ተጠቅሷል። ይልቁንም የሕዝቡ መጽሐፍ ነበር ስንል በግሪክ(አይሁዶች) ዘንድ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም በገሊላ እንዲሁም በይሁዳም ጭምር ነው እንጂ”[3]
ምንም እንኳን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ግን ኦሪጅናል ክታቡ ጠፍቶ ድጋሜ ኮፒ[4] የተደረጉ የኮፒ ኮፒ ኮፒዎች ቀሩ። ስለዚህም በዛ ሰዓት ስለነበረው የዕብራይስጥ መጽሐፍ ስናስብ ኦሪጅናል ብለን ልናስብ አይገባም። በጎን ደግሞ ይህ የግሪኩ ትርጓሜ ጥንታዊ ከመሆኑና በራሳቸው በአይሁዳውያንም የተመሰከረለት ከመሆኑ አንጻር ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። ለዛም ነው ከላይ እንዳየነው በሐዲስ ኪዳንም በክርስቶስና በሐዋርያቱ ዘንድ ጥቅም ላይ ውሎ የምናገኘው። እስከዛሬም ድረስ እኛ ክርስቲያኖች ይህንኑ መጽሐፍ እንቀበለዋለን። ታድያ ግን ቤተ ክርስቲያን ከተመሰረተች በኋላ ብዙ ክርስቲያኖች ሐዋርያትንም ጨምሮ የግሪኩን ብሉይ ኪዳን መጽሐፍ እየጠቀሱ ስለ ኢየሱስ መሲሕነት ማስረዳት ጀመሩ ብዙ አይሁዳውያንንም ወደ ክርስትና መለሱ። በዚህ ጊዜ ነበር አይሁድ አስቀድማ ክርስቶስን እንደገደለች በኋላም ሐዋርያቱን እንዳሳደደች እንደገደለችም፤ ጸረ ክርስቶስ ሆና ሰዎችን ወደ ክርስቶስ የሚመልሱትን የሐዋርያት የግሪክ መጽሐፍ ቅዱስን መቃወም ጀመረች። በሰዓቱ የዕብራይስጥ ቋንቋ በብዙ አይሁዳውያን ዘንድ በተዳከመበት በዛ ወቅት ሆን ብለው ክርስቲያኖችን ለመቃወም የግሪክ ሰብዓ ሊቃናቱን የራሳቸውን ትርጓሜ ማገድ ጀመሩ። ይህንንም በ2ኛው ክ/ዘመን የነበረው ሰማዕቱ ዮስቲን(Justin Martyr) በሰዓቱ ከነበረ አንድ የአይሁድ ሊቅ ጋር ባደረገው ውይይት(dialogue) ላይ አስፍሮታል።[5] በጣም የሚያስገርመን ግን የሰብዓ ሊቃናቱን ግሪክ አውግዘው ድጋሜ ለራሳቸው ደግሞ በሰዓቱ ካገኙት የኮፒ ኮፒ ዕብራይስጥ መጽሐፍ የግሪክ ትርጓሜ ማዘጋጀታቸው ነው። ከእነዚህም ውስጥ የአኪላ(Aquila)፣ የቴዎዶትዮስ(Theodotion)[6] እና የሲማከስ(Symmachus) ትርጓሜዎች ይገኙበታል። እነዚህም በአርጌንስ Hexapla በተሰኘው የብሉይ መጽሐፍ ስብስብ ሥራ ውስጥ ከሰብዓ ሊቃናት ጋር የተካተቱ ናቸው። አሁን ላይ የተወሰኑ ብጥስጣሾች(Fragments) ብቻ ነው ያሉት። አሁን ባለንበት ጊዜ ሆነን ስንመለከተው እነዚህ የግሪክ ትርጓሜያትም ሆኑ በዛ ሰዓት የነበረው እብራይስጥ መጽሐፍ ጥንታዊ ከመሆናቸው አንጻር ተቀባይነት ይኖራቸው ይሆናል ግን ደግሞ ሆን ብለው ያሳሳቱትንም ሆነ በኮፒስቶች ስህተት የገቡ ስህተቶቻቸውን ከግንዛቤ ውስጥ በመክተት ነው። በሰዓቱ ከነበሩ ስህተቶች ውስጥ አንዱ በትንቢተ ኢሳያስ 7፡14 ላይ የተጠቀሰው ሲሆን ይህም “ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች” በማለት መሲሕ ኢየሱስ ቀጥታ ውልደቱ ከድንግል እንደሆነ ከውልደቱ 700 ዓመት ቀደም ብሎ መተንበዩን ሲያመለክት ይህ ቃል ግን በዚህ መልኩ የሚገኘው የሰብዓ ሊቃናቱ ትርጓሜ ላይ ሲሆን ግሪኩ ታድያ ግን ክርስቶስ በተወለደበት ጊዜና ከዛ በኋላም የተገኙ የእብራይስጥ ኮፒ ክታባት “ድንግል” የሚለውን ቃል “ወጣት ሴት” ብሎት ተገኘ። ክርስቲያኖች የክርስቶስን በድንግልና መወለድ ከብሉይ ኪዳን ራሳቸው አይሁዳውያንም ከያዙት የግሪክ መጽሐፍ እየጠቀሱ ሲያስረዱ አይሁዳውያን ግን የሰብዓ ሊቃናትን አንቀበልም የእብራይስጡም ድንግል ሳይሆን “ወጣት ሴት” ነው የሚለው በማለት በእግዚአብሔር ቃል ላይ ማመጽን ተያያዙት። ይህም ደግሞ ከላይ በጠቀስነው ሰማዕቱ ዮስቲን ከታርፎን(ትሪፎን, Trypho) ጋር ባደረገው ውይይት ላይ የክርስቶስን በድንግልና መወለድ ዮስቲን ሲያስረዳው ትሪፎን የተባለው አይሁድ ግን ኢሳያስ 7፡14 “ድንግል” ሳይሆን “ወጣት ሴት” እንደሚል ሲሞግት እናየዋለን።[7] ይህም ብቻ ሳይሆን ክርስትና ከተጀመረ በኋላ ከእብራይስጥ ወደ ግሪክ የተተረጎሙት ከላይ ያየናቸው የእነ አቂላ እና ቴዎዶትዮን የግሪክ ትርጓሜዎችም ላይ “ወጣት ሴት” ብለው የተረጎሙት ሲሆን ይህንን ተከትለው ኢብዮናይት የተባሉ ቀደምት መናፍቃንም ክርስቶስ ከዮሴፍ ተወለደ ብለው ያምኑ እንደነበረ ጥንታዊው አባት ሄራንዮስ ይናገራል።[8] ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ከማርያም ድንግልና ጋር ተያይዞ ኢሳ 7፡14 ላይ ስላለው ቃል አንዳንደ ሰዎች ሌሎች ትርጓሜዎችን በማምጣት “ድንግል ሳይሆን ወጣት ሴት ነው የሚለው” የሚሉ እንደነበሩና ተዓማኒነት ያለው ግን ከክርስቶስ መምጣት በኋላ በጠላትነት ያደረጉት ትርጓሜ ሳይሆን ክርስቶስ ከመምጣቱ ብዙ ዓመታት በፊት የተረጎሙት የሰብዓ ሊቃናቱ ትርጓሜ ነው እያለ ያስረዳል[9]
ሰብዓ ሊቃናቱ ላይ ድንግል ተብሎ የተተረጎመው ቃል παρθένος(ፓርቴኖስ) የሚል ቃል ሲሆን አይሁዳውያኑ ግን ቃሉ መሆን የነበረበት νεᾶνις(ኔአኒስ) ነው ይላሉ። ይህም ከእብራይስጡ “አልማህ” ከሚለው ቃል ጋር እንዲስማማ ነው። በእርግጥ በእብራይስጥ “አልማህ” ተብለው የተጻፉ ብዙ ቦታዎች ላይ ግሪኩ “ኔአኒስ”(ወጣት ሴት) ብሎ ነው የተረጎመው። ታድያ እዚህ ክፍል ላይ ስለምን “ፓርቴኖስ”(ድንግል) ተብሎ ተተረጎመ የሚል አይጠፋም። ለዚህ የእኔን እይታ ለማስቀመጥ ያህል፡ አይሁዳውያን ገና ከጅምሩ ሲከራከሩ የነበሩት የኮፒ ኮፒ የሆነ እብራይስጥ መጽሐፍን ይዘው እንጂ ኦሪጅናሉን አግኝተውም አይደለም። እሱ ቀርቶ ያን ያህል ጥንታውያን ኮፒዎችንም ለመያዛቸው ማስረጃ የለም። እነሱ ከያዙት ኮፒ በእድሜ የሰብዓ ሊቃናቱ እንደሚቀድም ግልጽ ነው። ምክኒያቱም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ 300 ዓመት በፊት የተተረጎመና በአይሁዳውያንም ዘንድ ትክክለኛ እንደሆነ የተረጋገጠለት በራሳቸውም በአይሁዳውያን የተተረጎመ በመሆኑ። ስለዚህም ገና ከጅምሩ ኢሳያስ ትንቢቱን ሲናገር “ወጣት ሴት”(አልማህ) ብሎ ሳይሆን “ቤቱላህ”(ድንግል) በማለት ነው። ታድያ ግን በሰው ሰወኛው ለሚያስብ ሰው ድንግል ልትወልድ እንደማትችል ግልጽ ነውና አይሁዳውያን ከዚህ አንጻር ከጊዜ በኋላ ድንግል የሚለውን “ወጣት ሴት” ብለውታል የሚል እይታ አለኝ። ቃሉ ግን ቀጥታ “ድንግል” እንደሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ አለን። ይህም በሐዲስ ኪዳን በማቴዎስ ወንጌል ላይ መልአኩ ዮሴፍን ሲያጽናና እና ድንግል ማርያም ከወንድ እንዳልጸነሰች ሲያስረዳው ከትንቢተ ኢሳያስ በመጥቀስ “በነቢይ ‘እነሆ ድንግል(παρθένος) ትጸንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል’ የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆኗል” በማለት ነበር።(ማቴ 1፡23) ስለዛ ይህ ቃል በሃዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ ሲነገረን ማቴዎስ ራሱ የሰብዓ ሊቃናትን ትርጓሜ እንደሆነ የሚቀበለው እና እርሱ ብቻ ሳይሆን መልአኩም ሳይቀር የጠቀሰው በሰዓቱ ካለው እብራይስጥ ሳይሆን ከግሪኩ እንደሆነ ስንመለከት ችግር ያለው እብራይስጡ ጋር እንደሆነ እንረዳለን።
ቀለሜንጦስ ዘእስክንድርያ ስለ ሰብዓ ሊቃናቱ ትርጓሜ ሲናገር በእግዚአብሔር እቅድ ለግሪክ ሰሚዎች የሕግም የትንቢትም መጽሐፍት በሰባው ሊቃውንት እንደተተረጎመ ይናገራል።[10]
ቅዱስ ሄራንዮስ ሃዋርያዊ አባት እንዲህ ይላል “በነቢያቱ አድሮ ትንቢት ያናገረ በሰብዓ ሊቃናትም በትክክል ትንቢቱን ያስተረጎመ በሃዋርያትም የመንግስትን ወንጌል ያሳወጀ አንድና ተመሳሳይ መንፈስ ነው።”[11] በማለት ትርጓሜው ራሱ በመንፈስ ቅዱስ ተነሳሽነት እንደተተረጎመ ይናገራል። ይህ አባት የግሪክ ሰብዓ ሊቃናቱን ትርጓሜ አይሁዳውያን አንቀበልም ማለታቸውን አጥብቆ ይቃወምና ክርስቲያኖች ይህንን እየጠቀሱ ሲረቷቸው ይህንን ሃሳብ እንዳመጡም ይናገራቸዋል። ስለ ሰብዓ ሊቃናት ትርጓሜ ከተናገረው ነገር ውስጥ አንድ ልጋብዛችሁ፡
“መጽሐፍቱ(የሰብዓ ሊቃናቱ ትርጓሜ) እንዲህ ባለ ታማኝነትና በእግዚአብሔር ጸጋ ተተርጉመዋልና፤ ከእነዚህም መጽሐፍት ደግሞ እግዚአብሔር ለልጁ አዘጋጅቶናል፤ ብሎም እምነታችንን ሰርቷልናል፤ እንዲሁ ያልተበረዘን መጽሐፍ በግብጽ[12] ጠብቆልናል። ግብጽ፡ በከነዓን ከነበረው ረሃብ በሸሸ ጊዜ የያዕቆብ ቤት የታነጸበት፤ ጌታችንም ሄርዶስ ባሳደደው ጊዜ ሸሽቶ የተረፈበት.. (አሁን ደግሞ መጽሐፉን ጠበቀበት ነው)”[13]
በማለት በሰዓቱ ከነበረው የእብራይስጥ መጽሐፍ የግሪኩን ካስበለጠ በኋላ ዝቅ ሲል ደግሞ እንዲህ ይላል፡
“ሃዋርያት ጥንታውያን በመሆን አሁን ላይ ከተነሱ ሁሉ ምንፍቅና ቀድመው የነበሩት እነርሱ አስቀድመን ከተናገርነው ትርጓሜ ጋር ይስማማሉ፤ ትርጓሜውም ደግሞ ከሃዋርያት ትውፊት ጋር ይተባበራል። ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ፣ ማቴውስ፤ ጳውሎስ እንዲሁም ሌሎቹም፣ ተከታዮቻቸውም ትንቢታዊ ነገሮችን ሲሰጡን ሰባው ሊቃናት እንደተረጎሙት ነው።”
ከዚህ አንጻር የሰብዓ ሊቃናት ትርጓሜ ለቤተ ክርስቲያን ሃዋርያዊ ትውፊት(Apostolic
Tradition) ነው ማለት ይቻላል። ለምሳሌ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል “ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ። መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ”(ዕብ 10፡5) በማለት ይናገራል። ይህንን ቃል የሚናገረው ከመዝሙር 40፡6 በመውሰድ ሲሆን፡ “ሥጋን አዘጋጀህልኝ” የሚለው ሃረግ ግን የዕብራይስጡ መጽሐፍ ላይ አይገኝም። የሚገኘው ሰብዓ ሊቃናት(Septuagint) ላይ ነው።
ታድያ ግን እንዲህ እንዳለ ሆኖ በዛ ሰዓት የነበረው የእብራይስጥ መጽሐፍ በቅዱስ ጄሮም ጥቅም ላይ ውሎም እናገኘዋለን። ጄሮም በ5ኛው ክ/ዘመን አካባቢ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስን ቀጥታ ከእብራይስጥ ወደ ላቲን ተርጉሞታል ይህም የላቲን ትርጓሜ ቩልጌት(Vulgate) ይባላል። ጄሮም ይህንን የላቲን ትርጓሜ ሲሰራ ከእርሱ በፊት ግን ሌላ የላቲን ትርጓሜ ነበር ቬቱስ ላቲና(vetus latina) የሚባል። ይህ የቀደመው ላቲን ትርጓሜ የብሉይ ኪዳን መጽሐፉ የተተረጎመው ከሰብዓው ሊቃናት ነበር። በኋላ ግን ጄሮም ከጥቂት መጽሐፍት ውጪ ሌሎቹን የብሉይ መጽሐፍት ከእብራይስጥ ወደ ላቲን ድጋሜ ተረጎመው።ታድያ ግን እርሱ በነበረበት ሰዓት የነበረው አውግስጢኖስ ለጄሮም በላካቸው ደብዳቤዎች ውስጥ ትልቅ ስልጣን ያለው ሰብዓ ሊቃናቱ እንደሆነና ከእብራይስጥ ለምን መተርጎም እንዳስፈለገው ሲጠይቀው እንመለከታለን። ሁሉም አባቶች በሚባል ደረጃ ሲጠቅሱ የሚጠቅሱት ከሰብዓ ሊቃናቱ ግሪክ ነበር። ያም ሆነ ይህ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታላቅ ክብር የነበረው ከእብራይስጡ ይልቅ ግሪኩ እንደነበር ግልጽ ነው። ምናልባት ተጨማሪ ማስረጃ ይሆን ዘንድ ጥንታዊ በ4ኛውና 5ኛው ክ/ዘመናት ላይ በእጅ የተጻፉ እደክታባት(Manuscripts) ስንመለከት የብሉይ መጽሐፋቸው ግሪክ ሰብዓ ሊቃናት ናቸው። ከእነዚህም ጥንታውያን እደክታባት እነ ኮዴክስ ሳይናይቲከስ(codex sinaiticus)፣ ኮዴክስ ቫቲካነስ(codex vaticanus) እና ኮዴክስ አሌክሳንድሪነስ(codex alexandrinus) ይጠቀሳሉ።
ማጣቀሻ/References
[1] ሰብዓ ሊቃናት ስንል በፕሮቴስታንቱ ዓለም ተቀባይነት የሌላቸው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍትንም የሚያካትት ነው። [2] እዚህ ላይ “authorized version” በማለት የራሱን የተናገረው በፕሮቴስታንቱ አለም ለእነሱ authorized መጽሐፍ የሰብዓ ሊቃናቱ መጽሐፍ አይደለምና ነው። ምንም እንኳን ለእነሱ ባይሆንም በክርስቶስና በሐዋርያት ሰዓት ግን authorized መጽሐፍ የግሪኩ ነበር። [3] Edersheim, Alfred: The Life and Times of Jesus the Messiah: page 49 [4] ኮፒ ስንል ልክ እንደ አሁኑ በማሽን ሳይሆን በእጅ ድጋሜ በመጻፍ ነው። [5] Justin Martyr: dialogue with Trypho: chap. 71 [6] ይህ የግሪክ ትርጓሜ ቀጥታ ከእብራይስጥ ሳይሆን ራሱን ሰብዓ ሊቃናትን እንደ አዲስ አስተካክሎ ያዘጋጀው ነው የሚሉ አሉ [7] Ibid chap. 66 & 67 [8] Against Heresies 3: 21:1 [9] St. John Chrysostom: hom. On Matthew: 5:4 [10] The Stromata: bk. 1: chap. 22 [11] Ibid no. 4 (ሃሳቡን ቀጥታ በማስቀመጥ ጽሑፉን በትንሹ አሳጥሬዋለው) ከዚህም የምንረዳውሰብዓ ሊቃናትየተረጎሙት አምስቱንየሕግ መጽሐፍትብቻ ነው የሚለውንሃሳብ ይህ ጥንታዊአባት እንደማይቀበለውነው። እሱም ብቻ አይደለም ይልቁንም ከላይ እንዳየነው ሰማዕቱም ዮስቲንም አይቀበለውም። ሌሎቹም የብሉይ መጽሐፍት በራሳቸው እንደተተረጎሙ በ First Apology: chap. 31 ላይም ገልጾታል [12] “በግብጽ” ያለው የግሪኩ መጽሐፍ አስቀድሞ በበጥሊሞስ ትእዛዝ በግብጽ ስለተተረጎመ ነው። [13] Ibid no. 3
አኪ በጣም አሪፍ ርዕስ መርጠሀል።
እግዚአብሔር ይባርክህ።
thank