top of page

ትውፊት(παράδοσις-Tradition)

ትውፊት፡ ማለት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ውርስ ሲሆን በሁለት ከፍለን አንዱን ሰዋዊ ትውፊት ሌላውን ደግሞ ቅዱስ ትውፊት ልንለው እንችላለን። ሰዋዊ ትውፊት(ልማድ) የምንለው ከአምላክ መገለጥ ጋር የሚያያዝ ሳይሆን ሰዎች እንደ አካባቢያቸው የሚኖራቸውን ባህል ወይም ልማድ የሚያሳይ ነው። እንደማንኛውም አካባቢ አይሁዳውያንም የራሳቸው ልማድ እንደነበራቸው ግልጽ ነው። ለምሳሌ እጅን ታጥቦ መብላት ሰዋዊ ባህላቸው ነበር። ይህንን ልማዳቸውን ወይም ወጋቸውን ደግሞ ከአምላክ ቃል አስቀድመው ሲይዙትና ጌታ ኢየሱስም ሲወቅሳቸው በመጽሐፍ ቅዱስ እንመለከታለን(ማርቆስ 7)። ሌላኛው ሁለተኛው ትውፊት ደግሞ ቅዱስ(ክርስቲያናዊ) ትውፊት ነው። ይህ ደግሞ ከጌታ ጀምሮ በሐዋርያት በኩል ብሎም በአባቶች አንዱ ትውልድ ለሌላኛው ሲያስተላልፍ የኖረው የእግዚአብሔር አምላክ መገለጥ(Revelation) ነው። ትውፊት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ በግሪኩ ቋንቋ ፓራዶሲስ(παράδοσις) የሚል ሲሆን ቀጥታ ትርጉሙም “የትምሕርት ሽግግር(ከአንዱ ወደ ሌላው) ወይም ትውፊት” እንደማለት ነው።[1] “በቃል ወይም በጽሑፍ የተደረገን ነገር ማቀበል ወይም ማስተላለፍ” እንደማለትም ይሆናል።[2] ስለዚህም በአጭሩ አንዱ ትውልድ የተቀበለውን እምነት ለሚመጣው ትውልድ ደግሞ ሲያሸጋግር ማለት ነው።

በመጽሐፍ ቅዱሳችን በማቴዎስ 28፡19 ላይ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” በማለት ጌታችን ሲናገር እንመለከተዋለን። ለሐዋርያት አሕዛብን ሁሉ እንዲያጠምቁ አገልግሎት ሲሰጣቸው እስኪሞቱ ድረስ አብሯቸው እንደሚሆን በመናገር ሳይሆን እስከ ዓለም ፍጻሜ አብሯቸው እንደሚሆን በመናገር ነው። ታድያ ግን ሃዋርያት እስከ ዓለም ፍጻሜ ቆይተው ይህንን አገልግሎት የማያደርጉ ከሆነ በምን መልኩ እስከ ዓለም ፍጻሜ ክርስቶስ አብሮ ይሰራል ወይም ይኖራል ካልን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሃዋርያት ሲያልፉ ሌሎች ደግሞ በሃዋርያት በራሳቸው የተሾሙ አባቶች ስላሉ በእነሱ በኩል ጌታ ሥራውን ይቀጥላል። እነሱም ሲያልፉ ደግሞ ከእነርሱ በኋላ በሚነሱት አባቶች እያለ ሃዋርያዊ ቅብብሎሹን ጠብቆ እስከ ዓለም ፍጻሜ ጌታ ክርስቶስ በዝች ሃዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይሰራል። በምን መልኩ ይሰራል ካልን ስለሁላችን ሞቶ ከተነሳ በክብርም ካረገ በአባቱም ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ በመንፈሱ በኩል ከእኛ ጋር አንድ ይሆናል። በመንፈሱ በኩል ሁላችንን ክርስቲያኖችን ከእርሱ ጋር ያኖረናል(ሮሜ 8፡9)። ይሄ አንድነት ከትላንት ከሃዋርያት ጀምሮ እስከዛሬ ለወደፊትም እስከ ዓለም ፍጻሜ በዚህ መልኩ ሳይቋረጥ የሚቀጥል ሃይማኖት(እምነት)ነው። ከላይ በጠቀስነው ጥቅስ ላይ ጌታ “እያጠመቃችሁ” ብቻ ሳይሆን ያለው “ያዘዝኋችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው” ነውና “ትምሕርት” ደግሞ አለው። ይህም ትምሕርተ ሃይማኖት ነው። ይሁዳ በመልእክቱ ቁጥር 3 ላይ “...ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ” በማለት ይናገራል። እዚህ ጋር ይሁዳ ስለዚህ ሃይማኖት ይጽፍ ዘንድ ግድ የሆነበትን ምክኒያት ሲጽፍ ከሃዋርያት ትምሕርት የተለየ የምንፍቅና ትምሕርትን የሚያስተምሩ ሰዎች ሾልከው ገብተው ነበርና ነው። ስለዚህም ስለ ኃይማኖታችሁ ተጋደሉ በማለት ያገራል። ወደ ታች ደግሞ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ” በማለት በኃይማኖታችን ራሳችንን ለማነጽ እንድንተጋ ያስረዳል።(ቁጥር 20) ይህንን ከሐዋርያት ጀምሮ እየተላለፈ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተቀበልነውን እምነት ሐዋርያዊ ትውፊት እንለዋለን። ይህም ትውፊት በቃልም በጽሑፍም የተላለፈ ነው። ሐዋርያው እንደተናገረ እንዲህ ሲል፡ “በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ወግ(ትውፊት) ያዙ።”(2ተሰ 2፡15)

ታድያ ግን በፕሮቴስታንቱ አለም ትውፊትን እንደማይቀበሉና “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የእምነት መሰረት እንደሆነ ይናገራሉ። በተደጋጋሚም ሲናገሩ የምንሰማው “መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጽፏል..?? ካልተጻፈ አልቀበልም” ሲሉ ነው። ይህ አስተሳሰብ እንዲዲህ የሚያስፈልገን ሁሉ በመጽሐፍ ውስጥ ተጽፎልናል ብሎ ለመናገር ይመስላል። ይህንን ሃሳብ ፍጹም ሃሰት እንደሆነ በማሳየት ከሥር በሚኖረን ትምሕርት በሚገባ እናፈራርሰዋለን። “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚለው ትምሕርት ፈጽሞ ከክርስትና የተለየ አስተሳሰብ ነው። ምክኒያቱም የጌታ ፍቃድ ገና ከጅምሩ በመንፈሱ በኩል ከእርሱ ጋር አንድ ሆነን እንድንኖር እንጂ በመጽሐፍ በኩል እንድንኖር አልነበረምና። ቤተ ክርስቲያን ያለ መጽሐፍ ቅዱስ የኖረችበት ጊዜ አለ፤ የሃዲስ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት ቤተ ክርስቲያን ተመስርታ ብዙ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ካመኑ በኋላ ነው በራሷ በቤተ ክርስቲያን የተጻፉት። በተለይም ድንቅ የሆነው የዮሐንስ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ከተመሰረተች ሰባ አመታት በኋላ የተጻፈ ነው። ታድያ ግን ምንም እንኳን ያለ መጽሐፍ ቅዱስ መኖር ብትችልም ያለ መንፈስ ቅዱስ ግን ኖራ አታውቅም ልትኖርም አትችልም ምክኒያቱም ክርስቶስ ከቤተ ክርስቲያን ጋር አንድ ሆኖ የሚኖረው በመንፈሱ በኩል ነውና። ለዛም ነው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ[3] እንዲህ በማለት የሚናገረው፡ “እግዚአብሔር ሕዝቡን ማግኘት የሚፈልገው በመጽሐፍ ሳይሆን ቀጥታ በራሱ ነው.. እነ ኖኅን እነ አብረሃምን እንዲሁም ልጆአቸውን እንዳገኛቸው.. በኋላም ራሱን ሙሴንም በራሱ እንዳናገረው.. ከዛ በኋላ ግን ሕዝቡ ከእነርሱ የማይጠበቅ ኃጢዓትን ሲያደርጉ ግንኙነቱ በጽሑፍ ደግሞ ሆነ። ይህ ነገር ለሃዋርያትም ጭምር ነው.. ጌታ ወደ እውነት ሁሉ እንዲመራቸው ለሃዋርያቱ የሰጠው መጽሐፍን ሳይሆን ቅዱስ መንፈሱን ነው። በኋላ ግን ከዶግማ እና ከሕይወትም ጋር ተያይዞ ለማስታወሻነትም በጽሑፍ ሰፈረ።” በማለት ይናገራል። ከዚህም ደግሞ ክርስቶስ ለሐዋርያት የሰጠው መጽሐፍ ሳይሆን መንፈሱን እንደሆነ ልብ ልንለው ይገባል። መጽሐፉ የተጻፈው በፈሰሰላት መንፈስ በመነሳሳት በቤተ ክርስቲያን ነው። ስለ ትውፊት ምናልባትም ይህን ያህል ጠቅለል ያለ ሃሳብ ከሰጠን ሌሎች ማስረጃዎችን ከማስቀመጣችን በፊት በቅዱስ ትውፊት ሥር የሚካተቱት እነማን ናቸው የሚለውን ልናጠራ ይገባል። ያው ትውፊት ማለት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከጥንት ጀምሮ በቅብብሎሽ የመጣውን የቤተ ክርስቲያን ትምሕርትና ሥርዓትን እንደሚመለከት አይተናልና በዋናነት እነዚህን ሊያካትት ይችላል፡

- መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ(አዎ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ትውፊት ነው። ወደ ኋላ እንመለከተዋለን)

- የቤተ ክርስቲያን ጸሎቶች ወይም ቅዳሴያት(λειτουργία(ሌይቱርጊያ) – Liturgy)

- ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት ጋር የተስማሙ የቀደሙ አባቶች ጽሑፎች(writtings)፣ ስብከቶች(Homilies)፣ ትርጓሜዎች(commentaries, exegesis or expository works) እና የዕቅበት እምነት ሥራዎች(Apologetic works)

- የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት ላይ የተላለፉ ትምሕርቶች። ሦስቱ ዓለም አቀፍ ጉባኤያትን በትንሹ ለመጥቀስ ያህል፡


ጉባኤ ኒቂያ(325 ዓም)፡ አሪዮስ የተባለ መናፍቅ ወልድን ከአብ ለይቶ ፍጡር በመለኮቱ ብሎ ያስተማረ ሰው ነበር። የወልድን ውልደት ከመፈጠር ጋር በማገናኘት “ወልድ ሳይወለድ(ሳይፈጠር) በፊት ያልነበረበት ጊዜ ነበር በማለት ይናገር ነበር።

ታድያ ግን በኒቂያ የተሰበሰቡ ቅዱስ አትናቴዎስን ጨምሮ 318ቱ ቅዱሳን ሊቃውንት አባቶች ትምሕርቱን በመጽሐፍ ቅዱስና በሃዋርያዊ ትውፊት በመመዘን የቀለለና ታላቅ ኑፋቄ እንደሆነ በማመልከት አረሙን ከሰብሉ የለዩበት ጉባኤ ነው። በዚህም ጉባኤ ላይ ያረቀቁት የኃይማኖት ድንጋጌ(creed) አለ። ይህም እንደ አዲስ የረቀቀ ሳይሆን የነበረውን አጉልቶ ማሳየት ነበር።

ጉባኤ ቁስጥንጥንያ(381 ዓም)፡ በዚህ ጉባኤ “መንፈስ ቅዱስ ፍጡር ነው” ብሎ ያስተማረ መቅዶንዮስ እና ወልድ ሥጋን እንጂ ነፍስን የራሱ አላደረገም የሚል አቡሊኖርዮስ በቁስጥንጥንያ በተሰበሰቡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ እንዲሁም ቅዱስ ጢሞትዮስ ዘአልቦ ጥሪትን ጨምሮ 150 ቅዱሳን አባቶች በተገኙበት ምንፍቅናቸው የተወገዘበት ነው።

ጉባኤ ኤፌሶን(431 ዓም)፡ በዚህ ጉባኤ ጌታችን ኢየሱስን ሁለት አካልና ሁለት ባህሪ ብሎ ያስተማረ፤ በዚህም ምክኒያት ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ(Θεοτόκος- mother of God) አልልም ያለ ንስጥሮስ በኤፌሶን በተገኙ ቅዱስ ቄርሎስን ጨምሮ በሞቶ አባቶች የተወገዘበት ጉባኤ ነው።



ማጣቀሻ [1] Strong’s dictionary G3862 [2] Thayer's Greek Lexicon [3] Homilies on Mathew: Hom. 1 (በአጭሩ ነው ያስቀመጥኩት ሃሳቡን)

Recent Posts

See All
አሥር የ"መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ" ውድቀቶች

Ø መጽሐፍ ቅዱስ ብቻውን ስለራሱ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንኳን መልስ የለውም ለምሳሌ 4 ወንጌላት እንዳሉ ፕሮቴስታንቱ ያምናል። ወንጌላት 4 ብቻ ስለመሆናቸው ግን አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ የለም። ወይም ደግሞ 27...

 
 
 

Comments


​ከሥር ባለው ሳጥን ውስጥ ኢሜልዎትን በማስገባት "subscribe" የምትለዋን በመጫን አዳዲስ መልሶችን ቀጥታ በኢሜል ይቀበሉ

ቤተሰብ ስለሆኑን እናመሰግናለን

bottom of page