አሥር የ"መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ" ውድቀቶች
- aklil ዘኢየሱስ
- Apr 12, 2021
- 3 min read
Updated: May 20, 2021
Ø መጽሐፍ ቅዱስ ብቻውን ስለራሱ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንኳን መልስ የለውም ለምሳሌ 4 ወንጌላት እንዳሉ ፕሮቴስታንቱ ያምናል። ወንጌላት 4 ብቻ ስለመሆናቸው ግን አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ የለም። ወይም ደግሞ 27 የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት እንዳሉ ያምናሉ፤ ግን ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ የቱም ቦታ ላይ 27 የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት አሉ ብሎ አልተናገረም። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የሚለው ሰዋዊ ትምሕርት ውድቅ ሆነ።
Ø ፕሮቴስታንቶች መጽሐፍቱን ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንደተቀበሉ ያምናሉ። ታድያ ግን በእነርሱ ሃሳብ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ስህተት ሊሆን ይችላል የሚል ነው። ታድያ ስህተት የማይሆነውን(inffalible) መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት ሊሆን በሚችል(Fallible) ትውፊት እንዴት መወሰን ይቻላል? ምናልባት እንደ ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያንን የእውነት ሁሉ መገኛ ናት ብለው ካላመኑ በስተቀር።
Ø “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚል ትምሕርት ፈጽሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም በመጽሐፍ ቅዱስ አንድም ቦታ “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚል የለም። ይህ ማለት “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚለውን ትምሕርት በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ አያብራሩትም። “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” ብለው እየተናገሩ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን አንድም ድጋፍ የሌለው መሆኑን ስንመለከት ይህ ትምሕርት ሰዋዊ ብቻ ሳይሆን ሰነፍ_ሰዋዊ የሚያስብለውም እንደሆነ እንመለከታለን።
Ø ሦስተኛ ላይ ካነሳነው ጋር ተያይዞ፡ ታድያ ምነው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሌለ ሃሳብ ከሆነ ፕሮቴስታንቶች ሁሉ ለምን ተቀበሉት? የሚለውን ሃሳብ ስናነሳ ይህ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምሕርታቸው ለእነርሱ ሳያስቡት ትውፊት ሆኗል። የሚነሳው ሁሉ በሥላሴ የሚያምነውም የማያምነውም ፕሮቴስታንት “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን ከእርሱ ከሚቀድሙት ፕሮቴስታንት አባቶቹ በትውፊት ከተቀበለው ነውና ይህ ደግሞ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ትውፊትን በመቀበላቸው ከራሳቸው “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” ከሚለው ትምሕርታቸውም ጋር በሚገባ የሚጋጭ ነው።
Ø “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚለው ትምሕርት ታሪካዊም አይደለም። ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች የትውፊትን አስፈላጊነት አስቀምጠው አልፈዋል። ይህ ትምሕርት ግን የፕሮቴስታንቲዝም አባት ተብሎ በሚታወቀው በሉተር የተጀመረ ነው። ጅማሬውም የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት ከተጻፉ 1500 ዓመታት በኋላ በ16ኛው ክ/ዘመን ነው። ስለዚህም ይህ አባባል ሐዋርያትን ራሳቸውን ጨምሮ እስከ ሉተር ድረስ 1500 አመት ሙሉ የነበሩ ክርስቲያኖች ሁሉ ስህተት ውስጥ ወድቀው ነበር የሚያስብል ነው። ይህ ነገር ደግሞ ትክክል ከሆነ፤ እኛ ከሉተር ጋር ሆነን ትክክል ከምንሆን ከሐዋርያት ጋር ሆነን ስህተት መሆንን እንመርጣለን።
Ø ጴጥሮስ እንዲህ አለ፡ “በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም።” ታድያ ለገዛ ለራሱ ማንም አይተርጉም ከተባለ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ በራሱ ትርጓሜ አይደለምና ትርጓሜን ጥለው “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚሉ ሰዎች በዚህም ይረታሉ።
Ø ፕሮቴስታንቶች መጽሐፍ ቅዱስን ማንም ሰው በራሱ መተርጎም እንደሚችል ያስተምራሉ። ይህም ደግሞ የሚሆነው በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ እንደሆነም ይገልጻሉ። ለዚህ ንግግራቸው ምናልባት ጥያቄ እናንሳ ብንል፡ (??) ታድያ ምነው ፕሮቴስታንት የዚህን ያህል ተከፋፈለ? ለምንስ አንድ መሆን አቃተው? አንዱ የሚተረጉምበትስ መንገድ ከሌላኛው ለምን ተለያየ? ሁሉም ግን የሚሉት መንፈስ ቅዱስ እንደሚያስተምራቸው ነው። ታድያ አንዱ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይከፋፍላልን? ወይስ በእርግጥም ትርጓሜው ከአንዱ መንፈስ ቅዱስ ሳይሆን ከብዙዎች አጋንንታዊ መናፍስት? ምክኒያቱም ጳውሎስ አስቀድሞ የተናገረው ነገር ነበር፡ “መንፈስ ግን በግልጥ በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል፤ በገዛ ሕሊናቸው እንደሚቃጠሉ ደንዝዘው”(1ጢሞ 4፡1-2)
Ø በፕሮቴስታንቱ ዘንድ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ ብለው የጻፏቸው መጽሐፍት አሉ። ታድያ ግን “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” ካሉ “የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ” እያሉ ሌሎች ተጨማሪ መጽሐፍትን ማዘጋጀቱን ምን አመጣው? ይህም በዚህ በወጣው ማብራሪያ የሚመሩ ሁሉ ደግሞ የእርሱን ትውፊት የሚከተሉ እንጂ “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” ማለታቸውን ትተዋል ያስብላል።
Ø “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሱን ራሱ ከየት አመጡት..?? ከላይ እንዳየነው የሃዲስ ኪዳን መጽሐፍት ቀኖና እንኳን የተሰራላቸው በ4ኛው ክ/ዘመን ላይ ነው። ከዛ በፊት ግን በተለያዩ መጻሕፍት ላይ አጨቃጫቂ ነገሮች ነበሩ። ቤተ ክርስቲያን ግን በኋላ ላይ ይሄ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ብላ ሰጠች። ይሄ በቤተ ክርስቲያን በኩል የመጣው ትውፊት ፕሮቴስታንቶችም ጋር ደርሶ እነሱም የዚህ ትውፊት ተጠቃሚ ሆነዋል። ታድያ ትውፊት ይዞ “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” ማለት ምን ማለት ነው?
Ø በአጠቃላይ “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚለው ትምህርት በአሁን ሰዓት ከ40,000 በላይ ለሚሆኑ ለተከፋፈሉ የፕሮቴስታንት ቡድኖች መመስረት ዋናው ምክኒያት ነው።
Comments