ለቅዱስ ትውፊት ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስና በጥንታውያን አባቶች
- aklil ዘኢየሱስ
- Apr 12, 2021
- 4 min read
ማስረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስ፡
እንግዲህ ትውፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ብለን የተወሰኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶችን ከማስቀመጣችን በፊት ልንረዳ የሚገባን ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ትውፊት እንደሆነ ነው። ለምሳሌ ሃውርያው ጳውሎስ የዓይን ምስክር አይደለም፤ ከጌታም ሥር ተቀምጦ አልተማረም ግን በመንፈስ ቅዱስ በኩል ቀጥታ ከክርስቶስ ሃዋርያ በመሆን ትውፊትን እንደተቀበለ እናያለን። በ 1 ቆሮ 11፡23 ላይ “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን(ማቀበል) እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና(መቀበል)” በማለት እንደተናገረ። ትውፊት እንደምናውቀው በቃል(oral) የሚመጣና በጽሑፍ(written) የሚመጣ ነው፤ ሃውርያው “በቃልና በመልእክት የተማራችሁትን ትውፊት” እንዲል(2 ተሰ 2፡15)። ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ ከጽሑፋዊ ትውፊት(written tradition) የሚመደብ ነው። አንዳንድ ሰዎች “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” በማለት ትውፊትን አንቀበልም ማለታቸውን ስንመለከት ያስገርመናል። የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት ከተጻፉ በኋላ እንዲህ አሁን በያዝነው መልክ ተሰብስበው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ነው ተብሎ በቀኖና መልክ የተሰጠን ከሦስት መቶ አመታት በኋላ ነው። እስከዛ ድረስ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ምንም እንኳን canonized ባይደረግም አባቶች ግን በትውፊት መልክ በመውረስ ይጠቀሙበት ነበር። የሚያስገርመን ግን መጽሐፍቱ ተሰብስበው በቀኖና መልክ ሲዘጋጁ አንድም ኦሪጅናል መጽሐፍ አለመገኘቱ ነው። ጠቅላላ የተገኙት የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ዳግም በአባቶች በቅጂ(copy) መልክ የተጻፉ ናቸው። ታድያ ግን ምንም እንኳን ኦሪጅናል ጽሑፎች ባይገኙም አባቶች እነዚህ መጽሐፍት ከአባቶች ወደ እኛ የተላለፉ ናቸውና መጽሐፍ ቅዱስ ይሄ ነው ብለው ወሰኑ። እንግዲህ ሐዲስ ኪዳን ሲጻፍም በቤተ ክርስቲያን በኩል ነበር አሁንም ውሳኔ ሲተላለፍም በቤተ ክርስቲያኗ በኩል ነው። ይህ ሁሉ የሚደረገው ግን ቤተ ክርስቲያን ከሙሽራዋ ከክርስቶስ በተቀበለችው መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነው። በዚህ መልኩ የመጽሐፍ ቅዱስን ትውፊትነት ካየን እስቲ ደግሞ ከዚሁ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ቅዱስ ትውፊት ምን እንደተባለ ጥቅሶችን እንመልከት:
- 1 ቆሮ 11፡2 - ወንድሞች ሆይ፥ በሁሉ ስለምታስቡኝና አሳልፌ እንደ ሰጠኋችሁ ወግን(ትውፊትን) ፈጽማችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ።
- 1 ቆሮ 11፡34 - … የቀረውንም ነገር በመጣሁ ጊዜ እደነግጋለሁ።
(ይህ የቀረ የተባለው የሐዋርያት ድንጋጌ ሲደረግ በጽሑፍ የሰፈረ አይደለም። እንደምንመለከተው “በመጣሁ ጊዜ” በማለት በአካል ተገኝቶ እንደሚያደርገው ይናገራል)
- 2 ተሰ 2፡15 - እንግዲያስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጸንታችሁ ቁሙ፥ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ወግ(ትውፊት) ያዙ።
- 2 ተሰ 3፡6 - ወንድሞች ሆይ፥ ከእኛ እንደ ተቀበለው ወግ(ትውፊት) ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን።
- 2 ጢሞ 2፡2 - ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ። (በአደራ መልክ ከአንዱ ወደ አንዱ እየተላለፈ ስለመምጣቱ)
- ይሁ 3 - ...ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ። (ቅብብሎሽን ያሳያል)
- 2 ዮሐ 1፡12 - እንድጽፍላችሁ የምፈልገው ብዙ ነገር ሳለኝ በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልወድም፥ ዳሩ ግን ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ወደ እናንተ ልመጣ አፍ ለአፍም ልናገራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። (ቅዱስ ዮሐንስ ይጽፍላቸው ዘንድ የሚወደው ብዙ ነገር እንዳለ ያስቀምጣል። ታድያ ግን ከመጻፍ ይልቅ አፍ ለአፍ(በቃል) ይነግራቸው ዘንድ ደግሞ ተስፋ እንደሚያደርግ ይነግረናል። ስለዚህ ሃዋርያት ትምሕርታቸውን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያስተላለፉት በሁለቱም መንገድ እንደሆነ ያስረዳል)
- 3 ዮሐ 1፡13-14 - ልጽፍልህ የምፈልገው ብዙ ነገር ነበረኝ፥ ዳሩ ግን በቀለምና በብርዕ ልጽፍልህ አልወድም፤ ነገር ግን ወዲያው ላይህ ተስፋ አደርጋለሁ፥ አፍ ለአፍም እንነጋገራለን። (ቅዱስ ዮሐንስ በሚያስገርም ሁኔታ ደጋግሞ የሚናገረው ነገር ቢኖር ሊጽፍ የሚወደው ብዙ ነገር እንዳለና ይህም ማለት አሁን ጽሑፍ ላይ ያሰፈረው ጥቂት እንደሆነና የቀረውን ብዙውን ግን በጽሑፍ ሳይሆን በቃል "አፍ ለአፍ" እንደሚናገር ይገልጻል።)
ማስረጃ ከሃዋርያት በኋላ ከተነሱ አባቶች
የኒቂያው እና ቁስጥንጥንያው የእምነት ድንጋጌ(The holy Niceno-Constantinopolitan Creed)፡
በዚህ ላይ አባቶቻችን ያስቀመጥሉን “በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እናምናለን” የሚል ሳይሆን “አንዲት በምትሆን ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን” የሚል ነው።
ቅዱስ ሄራንዮስ(130-202 ዓም):
“እውነታው ያለው በዓለም አቀፋዊቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንጂ ሌላ በየትም አይደለም”[1]
ይህ ምድቡ ከሐዋርያዊ አበው(Apostolic Fathers) የሆነ አባት በተዘዋዋሪ በቅዱስ ፖሊካርፕስ በኩል ከዮሐንስ ወንጌላዊ የተማረ ሰው ነው። የእውነት ሁሉ መገኛን ሲናገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን ያለው ቤተ ክርስቲያን ነው ያለው። ምክኒያቱም የእውነት ሁሉ መሰረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናትና ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን ከተገኙ እውነታዎች ውስጥ አንዱ ነው። ሃዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ተመሳሳይ ነገር ሲናገር እንመለከተዋለን። እንዲህም አለ፡ “ብዘገይ ግን፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው።”[2]
በመቀጠልም ይህ አባት እንዲህ አለ፡
“እንበለውና በአስፈላጊ ጥያቄ ላይ በመካከላችን አለመስማማት ተፈጠረ። ታድያ ሃዋርያት አብዝተው ያዘወትሩባቸው ወደነበሩ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት በመመለስ አሁን ላይ ስለ ተነሳው ጥያቄ ግልጽ ማብራሪያ እናገኝ ዘንድ ከእነርሱ መማር የለብንምን? ምናልባት ሃዋርያት ያስተላለፉልን ጽሑፎች ባይኖሩስ ኖሮ፤ በቤተ ክርስቲያን በኩል ያስተላለፉትን ትውፊቶች እንከተል ዘንድ የግድ አይደለምን?”[3] ሄራንየስ እውነታው ያለው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብቻ እንደሆነ ሲናገርና ትውፊትን መቀበል እንዳለብን ሲሞግት ይህንን አቀረበ። በመቀጠልም እንዲህ አለ፡
“በክርስቶስ ያመኑ ብዙ የበርባርያን ብሔሮች፤ በወረቀትና ቀለም ያልሆነ ይልቁንም በመንፈስ ቅዱስ በልባቸው ላይ ተጽፎ እንዲሁም የቀደመውን የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት በጥንቃቄ ጠብቀው ድህነትን ያገኙ እነርሱ ተስማሙ”[4]
ቅዱስ ሄራንዮስ እዚው አካባቢ አያይዞ ከተናገረው ውስጥ አንድ እንጨምር:
“ከቫለንቲኑስ(Valentinus)[5] በፊት የቫለንቲኑስ ተከታዮች የሉም፤ እንዲሁ ከመርቅያኖስም(Marcion)[6] በፊት የመርቅያኖስ ተከታዮች የሉም።”[7]
በዚህ ገለጻው ላይ ደግሞ ድንቅ ነገር ያመለክተናል። ያው ከቫለንቲኑስ በፊት የቫለንቲኑስ ተከታዮች የሉም ማለቱ መስራቹ ወይም አስጀማሪው ራሱ ቫለንቲኑስ ነው ማለት ነው። ስለዛ ወደ ኋላ እስከ ሃዋርያት ድረስ ሊቆጥሩ አይችሉምና ሃዋርያዊ ሳይሆን የሚባሉት ቫለንቲኑሳውያን(Valentinians) ነው የሚባሉት። ይሄንን ነገር በመያዝ እኛም ደግሞ እንዲህ ልንል እንችላለን “ከሉተር በፊት የሉተር ተከታዮች የሉም” ስለዛ አሁንም ፕሮቴስታንቱ ሃዋርያዊ ሳይሆን የሚባለው ሉተራዊ፣ ካልቪናዊ እና ሌሎችም የፕሮቴስታንት ቤተ እምነት ቡድኖች መስራቾችን እየያዝን በእነሱ ልንጠራቸው እንችላለን ነው። ስለዛ ሃዋርያዊ የሚያስብለው መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ መያዝ ሳይሆን ሃዋርያዊ ትውፊትንም መያዝ ነው።
ቅዱስ አትናቴዎስ፡
“ሁላችን በክርስቶስ ክርስቲያኖች ስንባል፤ መርቅያኖስ የምንፍቅና ትምሕርትን አነሳ ተወገዘም፤ መርቅያኖስን ያወገዘውን የተከተለ ክርስቲያን እንደሆነ ሲቀጥል ከመርቅያኖስ ጋር አብሮ የወጡት ግን ክርስቲያን መባላቸው ቀርቷል ይልቁንም መርቅያኖሳዊ(Marcionites) ይባላሉ እንጂ። ልክ እንዲሁ ሌሎች መናፍቃንም ስማቸውን ለተከታዮቻቸው ሰጥተዋል። እንዲሁ እስክንድሮስ(Alexander) አርዮስን ሲያወግዝ ከእስክንድሮስ ጋር የቀሩት በክርስቲያንነታቸው ሲቀጥሉ ከአርዮስ ጋር የተለዩት ግን የጌታችንን ስም ለእኛ በመተው እነሱ አርዮሳውያን(Arians) ይባላሉ”[8]
(እንዳይበዛ ምንም የሃሳብ ለውጥ ሳላደርግ አሳጥሬዋለው) ሃሳቡ ደግሞ ከላይ ከጠቀስነው ከሄራንዮስ ጋር ተመሳሳይነት አለው። መጽሐፍ ቅዱሱን መቀበል ብቻ ክርስቲያን አያስብልም። ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱሱን በቤተ ክርስቲያኗ በኩል(በእሷ ትርጓሜ) ሲቀበል ነው ክርስቲያን የሚያስብለው።
ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፡
“..በቅብብሎሽ(succession) ውስጥ ከአባቶች የተቀበልነውን ትውፊት ለሁል ጊዜ አጥብቀን መያዝ አለብን..”[9] ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ፡ “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠብቆ የመጣውን እምነት(δόγμα – dogma) አንዳንዱን በጽሑፍ ተቀበልን ሌላውን ደግሞ በሃዋርያት ትውፊት ወደ እኛ የደረሰውን ተቀበልን። ከእውነተኛው ሃይማኖት አንጻር ሁለቱም ተመሳሳይ ሃይል አላቸው”[10]
“በመስቀል ምልክትስ እንድናማትብ ማን በጽሑፍ አስተማረን...... ይልቁንም በቃል ከተላለፈው ደግሞ ወሰድን”[11] ቅዱስ ኤጲፋኒዮስ፡ “ሁሉም ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝምና ትውፊትን የግድ ልንጠቀም ይገባል። ቅዱሳን ሃዋርያትም የተወሰኑትን በጽሑፍ ሌሎችን ደግሞ በትውፊት አቀብለውናልና።”[12] ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡ “ጳውሎስ እንዲህ በማለት አዘዘ ‘እንግዲያስ ወንድሞች ሆይ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ትውፊት ያዙ’[13] ከዚህም ሁሉን ነገር በመልእክታቸው እንዳላስተላለፉና ይልቁንም ብዙ ያልተጻፉ እንዳሉ ግልጽ ነው። በጽሑፍ እንዳሉት ሁሉ ያልተጻፉትም ደግሞ እምነት የሚጣልባቸው ናቸው።”[14]
ቅዱስጄሮም፡“ከዓለምጫፍከኢትዮጵያድረስየንግስቷንቦታጥሎወደቤተመቅደስየመጣው፤በሰረገላውስጥሆኖእንኳንሳይቀርመጽሐፍቅዱስንያነብየነበረየመለኮታዊእውቀትታላቅአፍቃሪየሆነውቅድሱጃንደራባ(ቅዱስባኮስ)ከኢሳያስትንቢትያነብነበርታድያግንስለማንእንደሚያወራእንኳንአያውቅምነበር።ሳያውቀውበመጽሐፍውስጥአመለከው..ፊሊጶስምአገኘውየሚያነበውንምገለጠለት..መጽሐፍቅዱስብቻውንሊያሳድገንአይቻልምየሚመራንከሌለበስተቀር(እንደቅዱስባኮስ)”[15]
አውግስጢኖስ:“የዓለምአቀፋዊቷቤተክርስቲያንድምጽባያሳምነኝኖሮበወንጌልምባላመንኩነበር”[16]
ማጣቀሻ(Reference) [1] Against heresies 3:4 [2] 1ጢሞ 3፡15 [3] Against heresies 3:4:1 [4] Against heresies 3:4:2 [5]ቫለንቲኑስ ድኅነት በእውቀት ዓይነት ትምሕርት የነበረው ኖስቲክ ነው። ሄራንዮስም በስፋት ለዚህ ሰው መልስ ሰጥቷል [6]መርቅያኖስ ደግሞ የብሉይ ኪዳንን አምላክ ክርስቶስን ከላከው ጋር በመለያየት ክርስቶስን የላከው አምላክ በብሉይ ከነበረው አምላክ ይበልጣል በማለት ያስተምር ነበር። [7] Against heresies 3:4:3 [8] Four discourse Against Arians: Discourse 1:chap. 1: 3 [9] On “Not Three Gods.” To Ablabius: par. 3 [10] On the Holy spirit: Chap. 27፡66 [11] Ibid [12] Panarion: 61:6(5) [13] 2 ተሰሎንቄ 2፡15 [14] Homilies on 2 Thessalonians 2:15, hom. 4 [15] Letter 53 To Paulinus: 5-6 [16] Contra Epist. Manichae quam V Cant Fundamentals (Fr Tadros Malaty – Tradition and orthodoxy)
Commentaires