ቁርአን በእስልምና
- aklil ዘኢየሱስ
- Apr 12, 2021
- 4 min read
- መጽሃፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል በሰዎች አንደበት እንደሆነ ይታወቃል.. ይህም ማለት ቃለ እግዚአብሔር ቢሆንም የጻፉት በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩ ቅዱሳን ሰዎች ሲሆኑ ሲጽፉም ከተገለጠላቸው ሳይወጡ ሰው በሚረዳው መልኩ አድርገው ነው። ስለዚህም እነዚህን መጽሐፍት ሃዋርያው ጳውሎስ “θεόπνευστος”(ቴዮኑስቶስ) በማለት ይጠራቸዋል.. “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት” ወይም ደግሞ እስትንፋሰ እግዚአብሔር እንደማለት ነው። ቁራን ግን የሚነገርለት ቀጥታ የቃላት አጣጣሉ ሳይቀር ከአላይ እንደወረደና ምንም አይነት የሰው እጅ እንዳልገባበት ነው። ሌላው ልናስታውሰው የሚገባው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቅዱሳን ሰዎች ነቢያትና ሃዋርያት በኩል የተገለጠ ሲሆን ቁራን ግን ሙሉውን በአንድ ሰው(መሃመድ) በኩል የተገለጠ ነው ብለው ያምናሉ። ቁርአን በሙስሊሞች ዘንድ ትልቅ ቦታ አለውና ስለ ቁርአኑ ያላቸውን እምነት እንደመግቢያ እንመልከት፡
ቁርአን አንዳንዴ በደወል ድምጽ አንዳንዴም በመልአክ በኩል ከአላህ ዘንድ በቃል ይገለጥለት እንደነበርና ከባዱም መገለጥ በደወል መልኩ የሚመጣው እንደሆነ የኢስላም መዛግብት ይናገራሉ(sahih bukhari vol. 1, bk. 1, no. 2)
ቁራኑም የወረደው በአረብኛ ቋንቋ ነበር.. “እኛ ፍቹን ታውቁ ዘንድ ዐረብኛ ቁርአን ሲሆን በእርግጥ አወረድነው” (ቁርአን 12፡2)
ቁርአን በተለምዶ የተጻፈውም መጽሐፍ መጠሪያ ሲሆን ቁርአን ግን recitation ነው። ማለትም እንዲሁ በአእምሮ የተያዘ የቃል ንባብ ማለት ነው። የተጻፈው መጽሐፉ ደግሞ “Mushaf” ይባላል ክታብ ወይም መጽሐፍ እንደማለት ነው።
ይህ ከአላህ ዘንድ ወረደ የሚባለው ቁርአን ከእኛ ሃዲስ ኪዳን የተወሰነ አነስ ያለ ሲሆን ሙሉ መጽሃፉ በምዕራፍ የተከፋፈለ ነው። የቁራን ምዕራፍ “ሱራ” ሲባል አንቀጹ ደግሞ “አያ” ይባላል። በአጠቃላይ 114 ምዕራፎች(ሱራዎች) ሲኖሩት እያንዳንዱ ምዕራፎች የተለያየ መጠን ያላቸው አንቀጾችን ይዟል።
እነዚህ 114 ምእራፎችም የየራሳቸው ስሞች ተሰጥቷቸዋል። ከእነዚህም ስሞች እንደ ምሳሌ ያህል፡ የሩዋጮች ምዕራፍ(100)፣ የረጋ ደም ምዕራፍ(96)፣ በብዛት የመፎካከር ምዕራፍ(102) እና የሸረሪት ምዕራፍ(20) ይጠቀሳሉ። እነዚህም ስሞች የወጡት በምእራፉ ውስጥ ከተገለጹት ነገሮች አንጻር ወይም ከምእራፉ ይዘት አንጻር እንደሆነ ይነገራል።
የቁራን ሱራዎች አንዴ የወረዱ ሳይሆን በተለያየ ጊዜያት ተከፋፍለው የወረዱ ናቸው(የሌሊት ጉዞ ምእራፍ 17፡106)
የወረዱትም አስቀድሞ ከመሃመድ ጉዞ በፊት በመካ እና ከጉዞ በኋላ በመዲና ነው.. ከዚህም አንጻር የቁራኑን ምእራፎች በሁለት ከፍለን የመካና የመዲና ልንላቸው እንችላለን።
መሃመድ ለመጀመሪያ ጊዜ ቁራን የወረደለት የአርባ አንድ አመት ሰው እያለ ሲሆን እስከ ሂጅራ(የመሃመድ ጉዞ ከመካ ወደ መዲና) ወይም ሃምሳ አራት አመት እኪሆነው ድረስ በተለያዩ ጊዜያት የወረደለት ሲሆን በአጠቃላይ በመዲናም ከወረደለት ጋር ቁርአኑ በሃያ ሦስት አመት ጊዜ ውስጥ እንደወረደ ይነገራል። ታድያ ግን በሳሂህ አል-ቡኻርይ [አሥር አመት መካ አሥር አመት ደግሞ መዲና እንደወረደና በሥልሳ አመቱ ጭንቅላቱ ላይ ጥቂት ጸጉሮች ሲቀሩ እንደ ሞተ ይናገራል] Sahih Bukhari: Volume 7, Book 72, Number 787
መሃመድ መገለጡ የጀመረው በመልካም ህልሞች እንደሆነና ከዛም ራስን አግልሎ የመቆየት ፍቅር ስላደረበት ራሱን ለማግለል ሂራ ወደ ተባለ ዋሻ የሚበላ ነገር ይዞ እየሄደ ይጸልይ እንደነበረና ከሆነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ወደ ሚስቱ ከድጃ(የመጀመሪያ ሚስቱ) በመመለስ የተወሰኑ ምሽቶችን ከእርሷ ጋር ካሳለፈ በኋላ በድጋሜ የሚበላው ነገር በመያዝ ወደዛው ዋሻ እየሄደ ይጸልይ ነበር ይባላል..(sahih bukhari vol. 1, bk. 1, no. 3)
ለመጀመሪያ ጊዜም ቁራን ወረደ የተባለው ከእለታት በአንድ ቀን በረመዳን ወር(የላም መራፍ 2፡185) በዋሻው ሳለ በመልአክ በኩል ወረደለት የተባለው አንቀጽ በቁራን የረጋ ደም ምእራፍ 96፡1-3 ላይ ያለው እንደሆነ ሲነገር( sahih bukhari vol. 1, bk. 1, no. 3) የመጀመሪያው ይህ የቁራን መገለጥም በሌሊት እንደሆነ ይነገራል(ቁራን 97፡1) ያችም ሌሊት “የመወሰኛ ሌሊት ወይም የከበረች ሌሊት” በመባል ትታወቃለች። ይህም አንቀጽ ከወረደ በኋላ ለ 3 አመት ያህል የወረደ አንቀጽ አልነበረም
ቁራኑ አንድ መጸሐፍ ሲሆን ግን ደግሞ ሙሉ በሙሉ አንዴ አለመውረዱ ምናልባት አላህ የሚመጣውን ነገር ጠንቅቆ ባለማወቁ በሰዓቱ ከሚፈጠሩ ሁኔታዎች አንጻር እንደ አየሩ ሁኔታ እያየ ለማውረድ ይመስላል.. የሚሉ አንዳንድ ሃሳቦች አሉ። ቁራኑ በሚወርደበትም ሰዓት ይህ ጥያቄ ከኢስላም ውጪ ካሉ ሰዎች ይነሳም እንደነበር ቁራን ይናገራል “እነዚያ የካዱትም ቁራን በእርሱ ላይ አንድ ጊዜ ለምን በጠቅላላው አልተወረደም አሉ” በማለት(ቁራን 25፡32)
መሃመድ በነበረበት ወቅት ቁራን በቃል ብቻ የሚባል እንጂ በጽሑፍ አልነበረም ማለት ይችላል። ምናልባትም የተወሰኑትን አንዳንድ ጸሐፊያን ለማስታወስ ያህል የተወሰኑ አንቀጾችን ካላሰፈሩ በስተቀር። ስለዚህም አሁን ላይ ሙስሊሞች እጅ የሚገኘውን ቁራን(ሙስሃፍ) መሃመድ ራሱም በዚህ መልኩ አያውቀውም ማለት ነው።
ይህ ብቻ ሳይሆን ቁራን ተሰብስቦ አሁን ባለው በሙስሃፍ መልክ የተቀመጠው በመሃመድ አዛዥነት አልነበረም። ከላይ እንዳልነው ጥቂት የቁራን ክፍሎች በጽሑፍ መልክ ተቀምጠው ቢሆንም አብዛኛው ግን ለመሃመድ ይወርድለታል በተባለው መልኩ በቃል ነበር በሰወች ዘንድ ተሸምድዶ የተቀመጠው። ታድያ ግን ለምን በሙስሃፍ መጣ..?? እንግዲህ ይህ የሆነበት ምክኒያት ቡኻሪይ በሃዲሱ እንዳስቀመጠውና ዛይድ ቢን ታቢት እንደተረከው መሃመድ ከሞተ በኋላ ቁራኑን ከመሃመድ ተምረው በቃል ሸምድደዋል የሚባሉ ተከታዮቹም በተለያዩ ጦርነቶች ውስጥ መሞት ይጀምራሉ። ታድያ ይህ ነገር ያሳሰበው ኡመር(Umar bin Al-Khattab) ወደ ወዳጁ አቡ በከር(Abu Bakr As-Siddiq) በመሄድ ቁራኑን የሸመደዱ ሰዎች እየሞቱ ስለሆነ ቁራንን ስለመሰብሰብ አወራው። ታድያ ግን አቡ በከር ሃሳቡን ሲሰማ መሃመድ ያላደረገው ነገር በመሆኑ ፍቃደኛ ባይሆንም አላህ ልቡን እንዳበራለትና እንደተስማማ ይናገራል.. ታድያ ይህንን ነገር ለዛይድ እንደነገሩትና እሱም በእነሱ ሃሳብ እንዲስማማና መሃመድም በነበረበት ሰዓት ከእርሱ ጋር በመሆን መሃመድ ሲያስፈልገው ይጽፍለት ስለነበረ ቁራኑን እንዲሰበስብ ይጠይቁታል። ታድያ ግን እሱም እንደ አቡ በከር እጅጉን በመደናገጥ “ይህንን ከሚያዙኝ ተራራን ግፋ ቢሉኝ ይቀለኛል” በማለት የነገሩን ክብደት በማንሳት “የአላህ መልእክተኛ ያላዘዙትን ያላደረጉትን እንዴት እናንተ ታደርጋላችሁ??” ብሎ ይጠይቃቸዋል በኋላም አላህ ልቡን እንዳበራለትና ከእነሱ ጋር እንደተስማማ.. ከዚህ በፊት ለማስታወሻነት የተጻፉትን እና በቃል ከሸመደዱ ሰዎችም በማሰባሰብ በአንድ እንዳደረገ.. የሱረቱ አል-ተውባህ የመጨረሻውን አያም እስኪያገኝ ድረስ እንደሰበሰበና ይህችንም አያ ከአቢ ኩዛይማ አል አንሳሪ(Abi Khuzaima Al-Ansari) ውጪ ማንም ጋር እንዳላገኛት ያስቀምጣል(ታድያ ግን የቁራን ክፍሎችን ከሰዎች ሲቀበሉ ቢያንስ የሁለት ሰው ምስክርነት ሊያቀርቡ እንደሚገባ አንዳንድ መዛግብቶች ቢያስቀምጡም ይህ የቁራን ክፍል ግን ከአንድ ሰው ብቻ እንጂ ሌላ ማንም ሰው ጋር እንዳልተገኘ በመናገሩ ቁራን ውስጥ እንኳን መካተቱ በሕገ ወጥ መልኩ ነው ያስብላል) ይህም የተሰበሰበው ቁራን በሙስሃፍ መልክ ሆኖ አቡ በከር ጋር ተቀመጠ እሱ ከሞተ በኋላም ኡመር ጋር እሱም ሲሞት ከሴት ልጁ ሃፍሳ ጋር ሆነ።(Sahih bukhari: vol. 6, bk. 61, no. 509)
ቁራንን ከመሰብሰብ ጋር በተያያዘ መሃመድ በነበረበት ሰዓት እንደተጀመረ የሚናገሩ ሙስሊሞች አሉ። ታድያ ግን ከላይም ሃዲሱ ባስቀመጠው መሰረት “መሃመድ ያላደረገውን እንዴት ታደርጋለህ” የሚልን ንግግር ከሁለት ሰው በመስማታችን ይህ ቁራንን የመሰብሰብ ነገር በመሃመድ ሰዓት ያልተደረገና እንግዳ የሆነ ነገር እንደነበር ግልጽ ነው። ታድያ ግን በመሃመድም ሰዓት ተጀምሮ እንደነበር የሚያሳይ ሁነኛ ማስረጃ አላገኘሁምና እዚህ ጋር ምንም ላስቀምጥ አልቻልኩም። ማስረጃ ቢኖርም ከላይኛው ጋር የሚጋጭ እንደሆነ ልብ ልንለው ይገባል ብዬ አስባለው።
ቁርአን ወደ መጽሐፍነት ከተቀየረ በኋላ ለብዙ አመታት በዛው ቁራኑ የወረበት ቋንቋ በተባለው በአረብኛ ቋንቋ የነበረ ሲሆን በኋላ ግን በ12ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ ላይ ወደ ላቲን ተተረጎመ ከዛም በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀምሪያ አካባቢ ለሕትመት በቃ። በኋላ ወደ ኢንግሊዘኛና ሌሎች የአውሮፓ ቋንቋዎች መተርጎም ተጀመረ። አሁን ላይ በስፋት በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ እናገኛለን። ለምሳሌ በአማርኛም።
እንደምናውቀው መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ቋንቋ ቢተረጎም(በተለይ በቤተ ክርስቲያን ሥልጣን) እስትንፋሰ እግዚአብሔርነቱ አይለወጥም” ስለዚህም የእብራይስጥና የግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ከእርሱ በኋላ የመጡ ጥንታውያን ትርጓሜዎች አሁን ላይ ያሉትን ጨምሮ እነ አማርኛና ኢንግሊዘኛን ትርጓሜ ሁሉም “ቃለ እግዚአብሔር በሰዎች አንደበት” ነው የሚባሉት። ታድያ ግን ይህ ማለት በህትመት ወቅት ወይም ሲተረጎም አንዳንድ ስህተት ሊገባበት አይችልም ማለት አይደለም.. ይህ አይነት ነገር ሲገጥም ግን ባለ ሥልጣኗ ቤተ ክርስቲያን ናትና ያለውን ችግር ታሳውቃለች። ቁርአን ግን በአረብኛ ቋንቋ እስከተጻፈና እስከታተመ ድረስ ብቻ ነው የፈጣሪ ቃል የሚባለው። ይህ ማለት ወደ ሌላ ቋንቋ ከተተረጎመ የአላህ ቃልነቱን ያጣዋል። ስለዚህም ለምሳሌ በሃገራችን ያሉ አረብኛውን የማያውቁ ሙስሊም ወንድም እህቶቻችን አማርኛውን ቁራን ሲያነቡት የአላህን ቃል እያነበቡ አይደለም ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ትርጓሜዎች “የቁርአን ትርጉም” ተብለው ብቻ ይሰየማሉ።(ቅዱስ ቁርአን [አማርኛ] - ነጃሺ አሳታሚ ድርጅት 1997 [መቅድም])
ይህ እንግዲህ ስለ ቁርአን በእስልምናው ዘንድ በስፋት የሚታመንበት ሲሆን አንዳንድ ጥያቄዎችን ግን ስለሚያስነሳ በሌሎች ፖስቶች ላይ እንመጣለን እግዚአብሔር ይርዳን።
ማጣቀሻ/References ቅዱስ ቁርአን አማርኛ ነጃሺ አሳታሚ ድርጅት 1997
Sahih bukhari
Tafsir ibn kathir
The history of the Quran by Allamah abu
Commentaires